ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ


አዲስ አበባ ሚያዚያ 28/2015(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋሉ።

ሃዋሳ ከተማ ከሲዳማ ቡና ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ሃዋሳ ከተማ በ31 ነጥብ 8ኛ ሲሆን በአንጻሩ ሲዳማ ቡና በ21 ነጥብ 14ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ሃዋሳ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ በተመሳሳይ በሁለቱ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

በአንጻሩ ሲዳማ ቡና ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም ፤ሁለት ጊዜ ተሸንፏል ሶስት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ሃዋሳ ከተማ 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።


በ22ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር የመጨረሻ ጨዋታ በወልቂጤ ከተማና ቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይደረጋል።


ወልቂጤ ከተማ በ25 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ በ48 ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ የመሪነቱን ቦታ ላይ ተቀምጧል። 


ወልቂጤ ከተማ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፤ ሶስት ጊዜ ተሸንፏል አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።


ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች አራት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።


ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ያደረጉት ጨዋታ ሁለት አቻ በሆነ ውጤት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።


ቅዱስ ጊዮርጊስ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ከተከታዩ ባህር ዳር ከተማ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሰባት ከፍ ያደርጋል።


የአዳማ ቆይታውን ያጠናቀቀው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከዛሬ የ22ኛ ሳምንት የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች እስከ 27ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐግብሮች በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እንደሚካሄዱ የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም