ቀጥታ፡

በሕብረት ሥራ ማህበራት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቶን የሰብል ምርት ለገበያ ማረጋጋት ማቅረብ ተችሏል ---ኮሚሽኑ

ባህር ዳር ሚያዚያ 27/2015  (ኢዜአ) የሕብረት ሥራ ማህበራት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቶን የተለያዩ የሰብል ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ገበያውን የማረጋጋት ሥራ መስራታቸውን የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ያለፉት ዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸምን ከክልል ህብረት ሥራ ሴክተር ጋር በባህር ዳር ከተማ እየገመገመ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አብዲ ዑመድ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ እንደ ሀገር ከ25 ሚሊዮን በላይ አባላት ያሏቸው ከ106 ሺህ 400 በላይ መሰረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒየኖች ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።  

ህብረት ሥራ ማህበራቱ በየአካባቢው ሻጭና ሸማቹን በማገናኘት በገበያው የተስተዋለውን የዋጋ መናር ለማረጋጋት እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

ለእዚህም ኤግዚቢሽንና ባዛር በማዘጋጀት የሰብል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የእንስሳት ተዋፅኦ ምርቶችን በማቅረብ ሰፊ ሥራ እየሰሩ መሆኑን ነው የገለጹት።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ገበያን ለማረጋጋት በህብረት ሥራ ማህበራት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን የሰብል ምርት ለማቅረብ ታቅዶ 93 ነጥብ 3 በመቶ ያህሉን ማከናወን እንደተቻለ አቶ አብዲ ገልፀዋል።

በቂ የሰብል ምርት ቢኖርም ማህበራቱ ምርቱን በብዛት ገዝተው እንዳያመጡ ገንዘብ ዋነኛ ማነቆ እንደሆነባቸው ገልጸው፣ "የገንዘብ ችግራቸውን ለማቃለልም ኮሚሽኑ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እየሰራ ይገኛል" ብለዋል።

ህብረት ሥራ ማህበራት በዋጋ የመደራደር፣ በገበያው ውስጥ የመወሰን አቅምና የተሻለ ድርሻ እንዲኖራቸው በቀጣይ የሪፎርም ሥራ እንደሚከናወንም አስታውቀዋል።

በግብርና  ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳሁን በበኩላቸው የህብረት ሥራ ማህበራት የግብርና ምርቶችን በማገበያየት አርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችና ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብም ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ሚናቸው የጎላ እንደሆነም ዶክተር ሶፊያ ተናግረዋል። 

"ይህም የግብርና ምርታማነት እንዲያድግ ከማገዝ ባለፈ ጥራቱን የጠበቀ የሰብል ምርት ሰብስቦ ለገበያ ለማቅረብ ጠቀሜታው የጎላ እንዲሆን ያደርጋል" ብለዋል።

አርሶ አደሩ ለሰብል ምርቱ ተገቢውን ዋጋ አግኝቶ ተጠቃሚ እንዲሆንና ገበያው እንዲረጋጋ በየደረጃው የሚገኙ የሕብረት ሥራ ማህበራት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩም ዶክተር ሶፊያ አሳስበዋል። 

በበጀት ዓመቱ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሰብል ምርት ወደገበያ በማስገባት ዋጋ ለማረጋጋት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ህብረት ሥራ ባለስልጣን ሃላፊ አቶ ጌትነት አማረ ናቸው።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ1 ሚሊዮን 254 ሺህ ኩንታል በላይ የተለያዩ የሰብል ምርቶችን ከአርሶ አደሩ በመግዛት ለገበያ ማረጋጋት ሥራ እንዲውል መደረጉን ገልጸዋል።   

የህብረት ሥራ ማህበራት ዋነኛው ማነቆ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጌትነት፣  "ችግሩን ለመፍታት እንደ ክልል 118 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ብድር ተመቻችቶ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

በመድረኩ የኮሚሽኑና የክልሎች የ2015 የዘጠኝ ወራት ሪፖርት ቀርቦ እየተገመገመ ሲሆን በነገው እለትም ለቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መድረኩ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም