ኢትዮጵያ በፈተናዎች ውስጥ ያሳካቻቸው የልማት ስራዎች መንግስት የገባውን ቃል በተግባር ለመፈጸም ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በፈተናዎች ውስጥ ያሳካቻቸው የልማት ስራዎች መንግስት የገባውን ቃል በተግባር ለመፈጸም ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ተጠቆመ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 27/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በፈተናዎች ውስጥ ያሳካቻቸው የልማት ስራዎች መንግስት የገባውን ቃል በተግባር ለመፈጸም ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ተጠቆመ፡፡
“ቃል፤ ተግባር፤ ትውልድ” በሚል መሪ ሐሳብ በአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት የመጽሐፍ ዐውደ ርዕይ ተካሂዷል።
በአውደ ርዕዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ 2010 እስከ 2013 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ያደረጓቸውን ንግግሮች የያዙና "ከመጋቢት እስከ መጋቢት" በሚል በሶስት ጥራዝ በተዘጋጁ መጽሐፍት ላይ ውይይት ተደርጓል።
በዚህም መጽሃፍቱ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተመዘገቡ ስኬቶች፣ ያጋጠሙ ፈተናዎችና በዋናነት በፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ ያተኮሩ ውይይቶች ተካሂደዋል።
በመድረኩ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው ግድቡ አሁን የደረሰበት ደረጃ የደረሰው በርካታ ፈተናዎችን አልፎ መሆኑን ተናግረዋል።
መንግስት ችግሮቹን በመፍታት ረገድ በቁርጠኝነት መስራቱንም ነው የተናገሩት፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ቤት የድህረ ምረቃ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አንተነህ ፀጋ በበኩላቸው በለውጡ ዓመታት በችግሮች ውስጥ በርካታ የልማት ስራዎችን መስራት ተችሏል ብለዋል።
እነዚህ የልማት ስራዎች ችግሮች ቢፈጠሩም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል የገቧቸውን ከመተግበር የሚያግድ ነገር አለመኖሩን በተግባር ያሳዩበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ለአብነትም ሀገሪቱ በግጭት ውስጥ በነበረችባቸው ጊዚያት ጭምር የልማት ስራዎች በጥራትና በጊዜ ተከናውነው እውን ሲሆኑ ማየት ተችሏል ብለዋል።
በለውጡ ዓመታት ቃል በተግባር የታየበት እና ቀጣዩን የብርሃን ዘመንም አመላካች የሆኑ ስራዎች እንደተሰሩ እንደሚያሳይ ዶክተር አንተነህ ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግሮች ዙሪያ ተሰንደው የተዘጋጁት መጻህፍት ፕሮጀክቶች በውጣ ውረዶች ውስጥም ቢሆን ስኬታማ መሆናቸውን የሚያመላክቱ መሆናቸውን ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው ገልፀዋል
መጽሃፍቱ በቀጣይም ለጥናትና ምርምር ስራዎች ግብዓት በመሆን በኩል ሚናቸው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በለውጡ በሁሉም ዘርፍ የተሰሩ ስራዎች ቃል በተግባር ያሳዩና ለመጪው ትውልድ አሻራ የሆኑ ስራዎች መሆናቸውን ነው ዶክተር አንተነህ ፀጋ የተናገሩት።