ቀጥታ፡

ወጣቱ ትውልድ ከጀግኖች አባቶቹ አንድነትንና የዓላማ ጽናትን ሊማር እንደሚገባ ተጠቆመ

ባህር ዳር ሚያዚያ 27 / 2015 (ኢዜአ): -''ወጣቱ ትውልድ ከኢትዮጵያዊያን ጀግኖች አርበኞች ሀገርን በመጠበቅ የዓላማ ጽናትንና አንድነትን ማወቅና ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል'' ሲሉ  የአማራ ክልል ጀግኖች አርበኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ዳኝነት አያሌው አመለከቱ።

በአገር አቀፍ ደረጃ ለ82ኛ ጊዜ የሚከበረው የኢትዮጵያ አርበኞች ድል መታሰቢያ በዓል በባህር ዳር ከተማ ተከብሯል።

በመጀመሪያው ዙር ወረራ ሽንፈቱ ያንገበገበው የጣሊያን ወራሪ ሃይል ለረጅም ጊዜ ሲዘጋጅ ቆይቶ ዳግም ኢትዮጵያን በመውረር የቅኝ ግዛቱ አካል ለማድረግ በ1928 ዓ.ም ወረራ መፈፀሙን ያስታወሱት ሊቀመንበሩ፤ ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች አርበኞች ዳግም ድል አድርገው የኢትዮጵያን ነጻነት አስጠብቀው መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች አርበኞች ይህንን ድል ያስመዘገቡት የዘር፣ የቀለምና የሃይማኖት ልዩነት ሳይበግራቸው ለአንዲት እናት አገራቸው ክብር የፀና ዓላማ በመያዝ እንደሆነ ገልፀዋል።

የአሁኑ ትውልድ ከጀግኖች እናትና አባቶቹ ሊማር የሚገባው የዓላማ ፅናትንና አንድነትን መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በበኩላቸው ቀኑ ሲዘከር ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች አንድነታቸውን ጠብቀው ያስመዘገቡትን ድል ዛሬም መድገም እንደሚቻል በማሳየት መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።

ኢትዮጵያዊያን አርበኞች በወቅቱ ዘመናዊ መሳሪያ ባይኖራቸውም በነበራቸው ከአለት የጠነከረ አንድነት የጣሊያን ወራሪ ሃይልን ማሸነፍ ችለዋል ብለዋል።

የአሁኑ ትውልድ በዘላቂነት የሃገር ችግር በሚፈቱ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩርም አስገንዝበው፤ ወጣቱ ትውልድ ችግርን በፅናት በመሻገር ሃገርና ህዝብ የሚያኮራ ታሪክ በመፃፍ ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ ወጣት ወርቁ ምንይበል ''እኛ ወጣቶች በተሰለፍንበት ሙያ በርትተን በመስራት ዘመኑ የሚጠይቀውን ጀግንነት ማስመዝገብ ይጠበቅብናል'' ብሏል።

በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሱና መዳረሻቸው የማይታወቁ መረጃዎች ሰለባ ባለመሆን እንደ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ታሪክ ማስመዝገብ እንደሚገባም ገልጿል።

በበዓሉ ላይ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ የጀግኖች አርበኞች አመራርና አባላት እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም