አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ፈተናዎችን በመቋቋም የተመዘገቡ የልማት ስኬቶች የኢትዮጵያዊያንን የትብብር አቅም በተግባር ያሳዩ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ፈተናዎችን በመቋቋም የተመዘገቡ የልማት ስኬቶች የኢትዮጵያዊያንን የትብብር አቅም በተግባር ያሳዩ ናቸው

አዲስ አበባ ሚያዚያ 27/2015(ኢዜአ)፡-አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ፈተናዎችን በጽናት በመቋቋም የተመዘገቡ የልማት ስኬቶች የኢትዮጵያዊያንን የትብብር አቅም በተግባር ያሳዩ መሆናቸው ተገለጸ፡፡
“ቃል፤ ተግባር፤ ትውልድ” በሚል መሪ ሐሳብ በአብርሆት ቤተ መጻሕፍት እየተካሄደ የሚገኘው የመጽሐፍ ዐውደ ርዕይ ዛሬም ቀጥሎ ውሏል።
በአውደ ርዕዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ 2010 እስከ 2013 ዓ.ም ባሉት ሶስት ዓመታት ያደረጓቸውን ንግግሮችን የያዙና "ከመጋቢት እስከ መጋቢት" በሚል በሶስት ጥራዝ በተዘጋጁ መጽሐፍት ላይ ውይይት ተደርጓል።
ውይይቱ በዋናነት በፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
በመድረኩም የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ፣የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ እና አርሶ አደር አሸናፊ አያሌው ሐሳባቸውን አካፍለዋል።
የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ኢትዮጵያ ያላትን ፀጋ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ የተለያዩ ውጤታማ ፕሮጀክቶችን ከቃል ወደ ተግባር መለወጥ መቻላቸውን ተናግረዋል።
አብዛኛዎቹ ስራዎች የተከናወኑት ደግሞ በኢትዮጵያ ያጋጠሙ በርካታ ፈተናዎችን በመቋቋም መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ በግብርና፣ በመንገድ በቱሪዝምና በሌሎች ግዙፍ ዘርፎች የተከናወኑ ሲሆን ግንባታቸውን በጊዜና በጥራት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል አሳይተዋል ብለዋል፡፡
ይህም የኢትዮጵያዊያንን የትብብር አቅም በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል፡፡
ዘመን ተሻጋሪ ሆነው የተሰሩት ስራዎች የሀገርን ገጽታ በመገንባት ረገድ ትልቅ ጥቅም እንዳላቸው አብራርተው እነዚህን ፕሮጀክቶች የተከናወኑበትን ሂደት ለትውልድ ሰንዶ ማስቀመጥ ተገቢ ነው ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በበኩላቸው፤ግድቡ የተለያዩ ፈተናዎች አልፎ ዛሬ ላይ መድረሱን ገልፀው ለዚህ ስኬት የመንግስት ቁርጠኝነት ወሳኝ እንደነበር አንስተዋል።
ግድቡ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ መድረሱ በፈተናዎች ውስጥ ፀንቶ መቆም እንደሚቻል ማሳያ መሆኑን ገልፀው ኢትዮጵያዊያን ጠንክረን የትኛውንም ችግር መቅረፍ እንደምንችል ግድቡ ማሳያ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን ግድቡን በመገንባቱ ሂደት ላይ ያሳዩትን አንድነት በሌሎች መስኮችም መድገም እንዳለባቸውም ነው ያመላከቱት፡፡
አርሶ አደር አሸናፊ አያሌው በበኩላቸው ከለውጡ ወዲህ መንግስት የወሰደው ቁርጠኝነት አርሶ አደሩ ተቀብሎ ተግባራዊ በማድረግ በግብርናው ዘርፍ ስኬቶች እንዲመዘገቡ ሆኗል ብለዋል።
ለአብነትም አርሶ አደሩ ከዚህ ቀደም በዓመት አንዴ ብቻ የሚያመርተውን ምርት አሁን በዓመት ሶስቴ እያመረተ ከራሱ አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሩን አንስተዋል።
መንግስት አርሶ አደሩን ከማምረት ባለፈ በገበያው ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን መስራቱ ትልቅ ተነሳሽነትን ፈጥሯል ብለዋል።