የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞቹን ከማጓጓዝ ባለፈ ምቹ ማረፊያ በመሆን የአፍሪካ ኩራትነቱን አስቀጥሏል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞቹን ከማጓጓዝ ባለፈ ምቹ ማረፊያ በመሆን የአፍሪካ ኩራትነቱን አስቀጥሏል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 27/2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞቹን ከማጓጓዝ ባለፈ ምቹ ማረፊያ በመሆን የአፍሪካ ኩራትነቱን አስቀጥሏል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አካል የሆነው የኢትዮጵያ የስካይ ላይት ሆቴል ምዕራፍ ሁለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ተመርቋል።
በመረሃ-ግብሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ ሚኒስትሮችና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ዲፕሎማቶች ታድመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዘመናት መካከል በተለዋዋጭ ሁኔታዎች ሳይበገር ከፍታውን አስጠብቆ የቆየ ተቋም ነው ብለዋል።
አየር መንገዱ በትውልድ ቅብብሎሽ አሁን በደረሰበት የእድገት ደረጃ ከሀገር አልፎ ለአፍሪካ ኩራት ሆኗል ነው ያሉት፡፡
አየር መንገዱ ደንበኞችን በማጓጓዝ መተላለፊያ ከመሆን ባሻገር ምቹ ማረፊያ ጭምር እየሆነ መምጣቱንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በተመሳሳይ ወቅት አገልግሎት መስጠት የጀመሩ በርካታ የአገር ውስጥ ተቋማት ቢኖሩም የአየር መንገዱን ያህል ማደግ አለመቻላቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያ ተቋማት እንደ አየር መንገዱ ሰፋ ያለ እቅድ በመያዝና ከሰፈር እይታ በመውጣት ከአገር ባለፈ በአህጉር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከ117 አመታት በፊት ጣይቱ ሆቴልን በመክፈት የሆቴል ኢንዱስትሪውን የተቀላቀለች ቢሆንም ዘርፉ በሚጠበቀው ልክ ሳያድግ መቆየቱን ገልጸዋል።
ነገር ግን ዛሬ የሚመረቀው የስካይ ላይት ሆቴል በኢትዮጵያ ሜጋ ሆቴሎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ መገንባት እንደሚቻል ያሳየና ለሌሎች ኢንቨስተሮችም በመሰል ስራዎች በስፋት እንዲሳተፉ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
በተጨማሪም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተሻለ መስህብ ባላቸውና ሊጎበኙ በሚችሉ አካባቢዎች አዳዲስ የፕሮጀክት ግንባታዎች እየተካሄዱ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ለአየር መንገዱ ተጨማሪ የገበያ ምንጭ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
በቅርቡ የተመረቀው የሃላላ ኬላ ሪዞርትን ፣ እንዲሁም በመጠናቀቅ ላይ ያሉት የጎርጎራ፣ ኮይሻና ወንጪ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ በቱሪዝሙ መስክ ውጤታማ እንደሚያደርጋት ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድም በተያያዘው ከፍታ እነዚህን ሆቴሎችና ሪዞርቶች በማስተሳሰር የበኩሉን ሚና እንዲወጣ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፣የምዕራፍ ሁለት ስካይ ላይት ሆቴል በአፍሪካ ከሚገኙ ሆቴሎች መካከል የሚጠቀስ ነው ብለዋል።
የአየር ትራንስፖርትና ቱሪዝም በከፍተኛ ደረጃ የተዛመዱ የስራ መስኮች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ አየር መንገዱ በአቪዬሽን መስክ እያስመዘገበ ያለውን ስኬት በቱሪዝሙም ለመድገም እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአየር መንገዱ ደንበኞች በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ የቱሪዝም ስፍራዎችን እንዲጎበኙ ከአጋር አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት መዲናዋን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም እንዲሁ፡፡
በዚህም የኢትዮጵያን ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህቦች ለመላው ዓለም በማስተዋወቅና አመቺ ዓለምና አቀፍ የሀገር ውስጥ በረራዎችን በማቅረብ እየሰራ ነው ብለዋል።