በወላይታ ዞን አረካ ከተማ በ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባ ድልድይ ተመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
በወላይታ ዞን አረካ ከተማ በ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባ ድልድይ ተመረቀ
ሶዶ፣ ሚያዚያ 27 / 2015 (ኢዜአ) በወላይታ ዞን አረካ ከተማ አስተዳደር ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባ ድልድይ ተመርቆ ለአገልግሎት በቃ።
በዕለቱ በ5 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ህንፃም ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።
በምርቃት ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የዞኑ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ዮሐንስ በየነ የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በአረካ ከተማ በልዩ ስሙ ሱታ መንደር ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ድልድይ ለአገልግሎት መብቃቱን ተናግረዋል።
የድልድዩ ግንባታ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ መጠናቀቁን ገልፀው፤ በተለይም ወቅቱ ዝናባማ በመሆኑ የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።
በሌላ በኩል በ5 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ህንፃም ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።
ከ2 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ በሆነ ቦታ የተገነባው የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች በተሰበሰበ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ መሆኑን ተናግረዋል።
ይሄም ለህብረተሰቡ አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመንና ለማቀላጠፍ አቅምን የሚጨምር ነው ብለዋል።
የአረካ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጴጥሮስ ወልደማርያም በበኩላቸው የድልድዩ አጠቃላይ ግንባታ በከተማው አስተዳደርና በአካባቢው ማህበረሰብ ድጋፍና ተሳትፎ የተገነባ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ ድልድዩ የህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የነበረ መሆኑን አስታውሰዋል።
ለተማሪዎች ትምህርት ቤትና ለታካሚዎች ወደ ጤና ተቋማት በቀላሉ ለመድረስ የሚረዳ በመሆኑ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
በምረቃው ስነ ሥርዓቱ ላይ የዞኑና የከተማዋ አመራሮችና የአካባቢው ማህበረሰብ ተሳታፊ ሆነዋል።