ቀጥታ፡

ሚድዋይፎችን በእውቀትና ክህሎት በማጎልበት የእናቶችና ህጻናት ሞትን ለመቀነስ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል

አዲስ አበባ ሚያዝያ 27/2015 (ኢዜአ) ሚድዋይፎችን በእውቀትና ክህሎት በማጎልበት የእናቶችና ህጻናት ሞትን ለመቀነስ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ  እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ገለጸ።

ዓለምአቀፉ የሚድዋይፎች ቀን በዓለም አቀፍ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ31ኛ ”በአንድነት ከማስረጃ ወደትግበራ” በሚል በዘውዲቱ ሆስፒታል ተከብሯል፡፡ 

የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ምክትል ስራአስኪያጅ ኢብራሂም ይመር በዚህን ወቅት የእናቶችና ህጻናት ሞት ለመቀነስ የሚድዋይፎች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል።

ለዚህም የሚድዋይፎችን የትምህርትና አቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎችን በመስጠት መደገፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ማህበሩ በዘርፍ  የሚሰሩ  የጤና  ባለሙያዎች የተሻለ እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት ይዘው ተገልጋዮችን በክብር፣ በፍቅርና በርህራሄ እንዲያገለግሉ ከተለያየ አካላት ጋር እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት በመስጠት የእናቶችና ህጻናት ሞትን ለመቀነስ እየተከናወኑ ላሉ ተግባራት የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ዓለም አቀፉ የሚድዋይፎች ቀን መከበር ዋና ዓላማም ሙያተኞች ለእናቶችና ህጻናት ሞት ቅነሳ ያቸውን ሚና ለማጉላት እንደሆነ ገልጸዋል።

የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ዶክተር ብርሃኑ አበራ በበኩላቸው፤ የጤና አገልግሎትን በማሻሻል የእናቶች እና ህጻናት ሞትን ለመቀነስ ለሙያተኞች ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር 31ኛውን ዓለምአቀፉ ሚድዋይፎች ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ በቀጣይ ግንቦት ወር በሐረሪ ክልል እንደሚከበር ተገልጿል፡፡

በዚህ አገር አቀፍ መድረክ ጥናታዊ ጽሁፎች የሚቀርቡበት፣ በጤና ዘርፍ አገልግሎት መሻሻል አስተዋጽኦ ላበረከቱ  እውቅና የሚሰጥበትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ውይይት ይካሄዳል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር በኢትዮጵያ ሚድዋይፎችን የሚወክልና የእናቶችና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የድርሻውን በመወጣት ላይ የሚገኝ የሙያ ማህበር ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም