ቀጥታ፡

ሕብረት ሥራ ማህበራት ዋጋን ወሳኝ በመሆን አርሶና አርብቶ አደሩን ለመጥቀም መስራት አለባቸው

ባህር ዳር ሚያዚያ 27/2015  (ኢዜአ)  ሕብረት ሥራ ማህበራት ዋጋን መቀበል ሳይሆን ወሳኝ በመሆን አርሶና አርብቶ አደሩን ከደላላ ጣልቃ ገብነት በማላቀቅ ተጠቃሚ ለማድረግ መስራት እንዳለባቸው ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ከክልል ሕብረት ሥራ ሴክተር ጋር የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸምን ለመገምገም ያዘጋጀው መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳሁን የሕብረት ሥራ ማህበራት በሀገር የኢኮኖሚ እድገት ላይ ድርሻቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ ግብአቶች ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆኑ ማህበራቱ ሚናቸው የጎላ እንደሆነ ገልጸዋል።

በመሆኑም ማህበራቱ ዋጋን የሚቀበሉ ሳይሆን ዋጋን የሚወስኑ ሆነው በመንቀሳቀስ አርሶና አርብቶ አደሩን ከደላላ ጣልቃ ገብነት በማላቀቅ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆን በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

በተለይ አርሶ አደሩ ምርቱን ለሕብረት ሥራ ማህበራት በተሻለ ዋጋ በማቅረብ በድካሙ ልክ ሽጦ ተጠቃሚ እንዲሆን በየደረጃው የሕብረት ሥራ ማህበራት በትኩረት እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ጌታቸው መለሰ በበኩላቸው እንዳሉት ለሀገሪቱ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው እድገት የሕብረት ሥራ ማህበራት ድርሻ አላቸው። 

አርሶ አደሩ ከምርቱ ተጠቃሚ እንዲሆንና በገበያ ዋጋን በማረጋጋት በኩል ሕብረት ሥራ ማህበራት የጎላ ሚና እንዳላቸውም  አስታውቀዋል።


 

ማህበራቱ የአገር በቀል ኢኮኖሚ እንዲሻሻል ከማድረክ ባለፈ የአገር ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ እድገት እንዲፋጠን ትልቅ የኢኮኖሚ መሳሪያ ሆነው እያገለገሉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በገጠርና ከተማ ህብረተሰቡ በህብረት ሥራ ማህበራት ተደራጅቶ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቹን ለመፍታት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸው፣ ይህን ለማጠናከር ኮሚሽኑ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ ግብአቶችና የመካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎች በሕብረት ሥራ ማህበራት በኩል ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዶክተር ጌታቸው እንዳሉት የገበያ ዋጋ እንዲረጋጋ በማድረግ በኩልም ሕብረት ሥራ ማህበራት ሚናቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።

የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም መገምገሚያ መድረኩ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን በመድረኩ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በመድረኩ ከኮሚሽኑ፣ ከግብርና ሚኒስቴር እና ከክልሎች ሕብረት ሥራ ሴክተር የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም