በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ የነበሩ የትግራይ ክልል ክለቦችን በቀጣዩ ዓመት በሊጉ እንዲሳተፉ ለማድረግ እየተሰራ ነው -የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እግር ኳስ ፌዴሬሽን - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ የነበሩ የትግራይ ክልል ክለቦችን በቀጣዩ ዓመት በሊጉ እንዲሳተፉ ለማድረግ እየተሰራ ነው -የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እግር ኳስ ፌዴሬሽን
አዲስ አበባ ሚያዝያ 27/2015(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ የነበሩ የትግራይ ክልል ክለቦችን በቀጣዩ ዓመት በሊጉ እንዲሳተፉ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳሰ ፌዴሬሽን በበኩሉ የትግራይ ክልል ክለቦችን ወደ ሊጉ ለመመለስ ዓለም አቀፍ ህጎችን መሰረት ባደረገ መልኩ የባለድርሻ አካላት ውይይት እንደሚያደርግ ጠቁሟል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ነጋ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት በኮቪድ 19 ወረርሽኝና ከዚያ በኋላ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት የክልሉ ክለቦች ከውድድር ርቀው ቆይተዋል፡፡
አሁን ላይ ሰላም መፈጠሩን ተከትሎ የክልሉን እግር ኳስ ክለቦች መልሶ ለማደራጀት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዋናነት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ የነበሩ ክለቦችን በቀጣዩ ዓመት በሊጉ ውድድር እንዲሳተፉ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ በታችኛው ሊግ ሲጫወቱ የነበሩ ሌሎች ክለቦች ደረጃ በደረጃ ወደ ነበሩበት ተመልሰው እንዲጫወቱ ለማድረግ እቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡
ከክለቦቹ ጋር በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ ውይይቶችም ወደ ሊጉ ለመመለስ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውን ነው የተናገሩት።
ነገር ግን ወደ ሀገራዊ የእግር ኳስ ውድድሮች ለመመለስ የገንዘብ አቅም ውስንነት እንዳለባቸውም አቶ ነጋ ተናግረዋል፡፡
ክለቦችን ወደ ውድድር ለመመለስና መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመጠገን የፋይናንስ አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት እገዛና ድጋፍ እንዲያደርጉላቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ፌዴሬሽኑ የክልሉን እግር ኳስ ለመደገፍና ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ቡድኖቹ በድጋሚ በሊጉ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ የእግር ኳስ ህጎችን በማየትና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ለጉዳዩ ምላሽ እንደሚሰጥም ተናግረዋል።
የሰሜኑ ጦርነት ከመከሰቱ በፊት በታችኛው ሊግ የሚሳተፉ የእግር ኳስ ክለቦችን ሳይጨምር መቐለ 70 እንደርታ፣ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲና ስሁል ሽረ የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ ክለቦች እንደነበሩ ይታወሳል።
መቐለ 70 እንደርታ የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮና ክለብ እንደነበር የሚታወስ ነው ፡፡