ጀግኖች አባቶች በመስዋዕትነት ከነክብሯ ያስረከቡንን ሀገር በልማት ፋና ወጊነት ልናስቀጥል ይገባል-ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
ጀግኖች አባቶች በመስዋዕትነት ከነክብሯ ያስረከቡንን ሀገር በልማት ፋና ወጊነት ልናስቀጥል ይገባል-ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ
ሀዋሳ ሚያዚያ 27/2015(ኢዜአ)፦ ጀግኖች አባቶች የህይወት መስዋዕትነት ከፍለው ከነሙሉ ክብሯ ያስረከቡንን ሀገር የአሁኑ ትውልድ አገራዊ ልማትን በማረጋገጥ ውለታቸውን መክፈል አለብን ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ 82ኛውን የኢትዮጵያ አርበኞች ድል መታሰቢያ በዓል በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም ጀግኖች አባቶች የሐገራቸውን ሉዓላዊነትና ክብር ለማስጠበቅ ከፋሺስት የጣልያን ወራሪ ሀይል ጋር በዱር በገደሉ ተዋድቀው ኢትዮጵያን ከነክብሯ አቆይተውልናል ብለዋል።
ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ታጥቆ የመጣው የጣልያን ወራሪ ሀይል ኋላቀር የጦር መሳርያ ያነገቡ አባቶቻችንን ማሸነፍ ያልቻለው አባቶች ከዓለት የጠነከረ አንድነት፣ ህብረትና የጋራ አገራዊ ፍቅር ስለነበራቸው መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡት ጀግኖች አባቶች በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ በፋሺስት ጣልያን ላይ ያስመዘገቡት ድል ዛሬ ድረስ የመላው ጥቁር ህዝቦች ኩራት መሆኑን ጠቁመዋል።
ጀግኖች አርበኞች ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት እና ማንነት ሳይለያቸው በአንድነት መንቀሳቀሳቸው ለድል እንዳበቃቸው የጠቀሱት ርዕሰ-መስተዳድሩ "ይህም ሕብረ-ብሔራዊነት የአሸናፊነት አቅም መሆኑን ያሳያል" ብለዋል።
አባቶቻችን ለሀገር ክብርና ሉዓላዊነት ሲሉ የከፈሉትን መስዋዕትነት ስንዘክር እኛም ለመጪው ትውልድ ክብሯንና ልዕልናዋን የጠበቀች ኢትዮጵያን ለማስረከብ በተሰማራንበት ሁሉ ስኬትን በማስመዝገብ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
"በተለይም አሁን እየተመዘገቡ ያሉ ታላላቅ ስኬቶችን በማጠናከር የዜጎችን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት መቆም ያስፈልጋል" ብለዋል።
"በዚህም ጀግኖች አባቶች ለሀገርና ለህዝብ ሲሉ ደምና አጥንታቸውን በመገበር የዋሉልንን ውለታ ልንከፍል ይገባል" ሲሉም ገልጸዋል።
የሀዝብን አንድነት በመሸርሸር ሀገራዊ የልማት ጉዞን ለማደናቀፍ የሚስተዋሉ የጽንፈኝነት ተግባራትን ማውገዝ እንደሚገባ የገለጹት አቶ ደስታ፣ ትውልዱ የአባቶቹን ፈለግ ተከትሎ ለሀገሩ ሉዓላዊነት፣ ክብርና ደህንነት ዘብ መቆም እንዳለበትም አመልክተዋል።