ቀጥታ፡

አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ታዳጊዎች ከታችኛው የትምህርት ደረጃ ጀምሮ በሙያና ክህሎት ጎልብተው እንዲያድጉ ያደርጋል

አዲስ አበባ ሚያዝያ 27/2015(ኢዜአ)፦አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ታዳጊዎች ከታችኛው የትምህርት ደረጃ ጀምሮ በሙያና ክህሎት ጎልብተው እንዲያድጉ እንደሚያደርግ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሻለ በሬቻ ገለጹ።

አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠናን በስርዓተ ትምህርት ውስጥ በማካተት ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሻለ በሬቻ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ከዚህ ቀደም ሲተገበር የቆየው የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ የቀለም ትምህርት ላይ ያተኮረ መሆኑ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ጥናት በተካሄደበት ወቅት መለየቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የአገር በቀል እውቀቶችን አለማካተቱ እንዲሁም ለሙያ ክህሎትና ለተግባር ስልጠና ትኩረት አለመስጠቱ ተመላክቷል።

የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ፖሊሲውን በማዘጋጀትና በማስፈጸም ረገድ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር መስራቱን በማስታወስ ፖሊሲው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ ተካቶ እንዲሰጥ ያደርጋልም ብለዋል።

በዋናነትም ተማሪዎች ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ድረስ ከቀለም ትምህርት ጎን ለጎን የሙያና የክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ ያስችላል።

በተጨማሪም ተማሪዎች ወደ መሰናዶ የትምህርት ደረጃ ሲሸጋገሩ የሙያ ትምህርትና ስልጠና ራሱን ችሎ ከቀለም ትምህርት ጎን ለጎን እንዲሰጥ ይደረጋል ነው ያሉት።

ይህም ዜጎች የቴክኒክና ሙያ ትምህርትን አልያም የሙያ ስልጠናን ከስር ጀምሮ እንዲለማመዱ በማድረግ በሙያው የሚተማመን ብሎም ቴክኖሎጂ መር እድገትን የሚያረጋግጥ ትውልድ ለመፍጠር እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

ለአዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ትግበራ፣የሙያተኞች፣የግብዓትና መሰል ተግባራት መሟላታቸውን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

በመሆኑም አዲሱ ፖሊሲ በሙከራ ደረጃ እየተተገበረ እንደሚገኝ ገልጸው  ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ በመላ አገሪቱ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንደሚሆን አረጋግጠዋል።

ፖሊሲውን ስኬታማ ለማድረግ የሁሉንም ባለ ድርሻ አካላት እገዛና ትብብር እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል።

አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ከአንድ ወር በፊት በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁ ይታወቃል። 

 

  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም