የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአህጉር አቀፍ ደረጃ እያስመዘገበ ያለው ስኬት ለሌሎች ተቋማትም ትምህርት የሚሰጥ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአህጉር አቀፍ ደረጃ እያስመዘገበ ያለው ስኬት ለሌሎች ተቋማትም ትምህርት የሚሰጥ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 27/2015(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአህጉር አቀፍ ደረጃ እያስመዘገበ ያለው ስኬት ለሌሎች ተቋማትም ትምህርት የሚሰጥ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ ያስገነባውን ምዕራፍ ሁለት ስካይ ላይት ሆቴል መርቀው ከፍተዋል፡፡
መረሃ-ግብሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ ሚኒስትሮች፣ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ዲፕሎማቶች ታድመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ ደንበኞችን ከማጓጓዝ ባሻገር ምቹ ማረፊያ ጭምር እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።
አየር መንገዱ በትውልድ ቅብብሎሽ አሁን ለደረሰበት እድገት ከሀገር አልፎ ለአፍሪካ ኩራት ሆኗል ነው ያሉት ፡፡
ሌሎች ተቋማትም ከአየር መንገዱ ስኬት ልምድ በመውሰድ ከአገር ባሻገር በአፍሪካም ተወዳዳሪ ለመሆን መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፣ ፣የምዕራፍ ሁለት ስካይ ላይት ሆቴል በአፍሪካ ከሚገኙ ሆቴሎች መካከል የሚጠቀስ ነው ብለዋል።
አየር መንገዱ በአቪዬሽን መስክ አሁን የደረሰበትን እድገት ከማስቀጠል ባሻገር አዲስ አበባን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ጭምር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል።
አየር መንገዱ ከቁጥር አንድ የስካይ ላይት ሆቴል በተጨማሪ ዛሬ ያስመረቀው ቁጥር ሁለት የስካይ ላይት ሆቴል አዲስ አበባን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የሚከናወኑ ተግባራት አካል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አዲስ የተገነባው ቁጥር ሁለት ስካይ ላይት ሆቴል በ11 ሺህ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን 651 የመኝታ ክፍሎች እንዳሉትም አብራርተዋል።
በተጨማሪም ዘመናዊ የስብሰባ አዳራሾች፣የጤና ማዕከል ፣ምግብ ቤቶችና የመዝናኛ ስፍራዎችን አካቷል፡፡
የሆቴሉ ግንባታ የተከናወነው "አቪክ" በተሰኘ የቻይና ህንጻ ተቋራጭ መሆኑም ተመላክቷል፡፡