ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ያላትን ልምድ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እንድታካፍል የአፍሪካ ሲዲሲ ጠየቀ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 27/2015(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ያላትን ልምድ እና የሰው ሀይል ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እንድታካፍል የአፍሪካ ሲዲሲ ጠየቀ።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አዲስ ከተሾሙት የአፍሪካ ሲዲሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዢን ካሴያን ጋር ተወያይተዋል።

በዚህ ወቅት የአፍሪካ ሲዲሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዢን ካሴያን ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ያላትን ልምድ እና የሰው ሀይል ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እንድታካፍል ጠይቀዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ሲወስድ የነበራቸዉን እርምጃዎች አድንቀዋል።

በተለይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወረርሽኙ በተከሰተበት ወቅት ለብዙ የአፍሪካ ሀገራት ህይወት አድን የሆኑ የጤና ቁሳቁሶችን በማድረስ በኩል ላበረከተው እስተዋጽኦ አድናቆታቸውን ለግሰዋል።

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሀገሪቱን የጤና ስርዓት ለማሻሻል እየተጫወተ ያለውን ሚና በተመለከተም ገንቢ አስተያየታቸውን ለግሰዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደስ በበኩላቸው ጤና ሚኒስቴር ከአፍሪካ ሲዲሲ ጋር በተለያዩ የህብረተሰብ ጤና ጉዳዮች ላይ በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በተለይ ክትባትን ተደራሽ በማድረግና ለማምረት በሚደረገዉ ጥረት እንዲሁም የጤና ስርአት በማጠናከር በኩል ያለዉ ትብብር ጠንካራ መሆኑም አስታውቀዋል።

በቀጣይም ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰራ ዶክተር ሊያ ገልጸው፤ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የሰው ሀብቷን ለማልማት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ማፍሰሷን አስታውሰዋል።

ዶክተር ሊያ አክለውም ኢትዮጵያ ልምዷን ከማካፈል ባለፈ ያፈራችውን የጤና ዘርፍ የሰው ሀብት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለማካፈል ዝግጁ ናት ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከአለም ባንክ እና አለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች እንዲሁም ከአፍሪካ ሲዲሲ ጋር በመተባበር ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም የሚጠቅም የክትባት ማምረቻ ለማቋቋም እየሰራች መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሲዲሲ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን ዶክተር ሊያ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም