አርበኝነት ትውልድን የምንቀርፅበት እሴታችን ነዉ -ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
አርበኝነት ትውልድን የምንቀርፅበት እሴታችን ነዉ -ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 27/2015(ኢዜአ)፦ አርበኝነት ትውልድን የምንቀርፅበት እሴታችን ነዉ ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።
82ኛ ዓመት የድል መታሰቢያ በዓል አብሮነት ለፅናትና ለድል በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ነው።
በመታሰቢያ በዓል አከባበሩ ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው፤ አባት እና እናት አርበኞች፣ የአርበኞች ቤተሰቦች ፣የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ አባላት፣ የተለያዩ አገራት ተወካዮችና የከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
በበዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለመላው ኢትዮጵያውያን ለአርበኞች የድል መታሰቢያ በዓል እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።
ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለው የአገራችንን ሉዓላዊነት ለአስከበሩ አርበኞችም ምስጋና አቅርበዋል።
አርበኝነት የዛሬውን ትውልድ ለነገ የምንቀርፅበት እሴታችን ነው ሲሉም ተናግረዋል።
አሁንም የሚያዚያ 27/1933 ዓም የአርበኞች የድል ታሪክን ስናከብር ለአሁኑ ትውልድ በጋራ በመስራት ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ትልቅ ማሳያ ነዉ ብለዋል።
የጥንታዊት የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዘዳንት ልጅ ዳንኤል መስፍን ጆቴ በበኩላቸው አባቶቻችን ያወረሱን ለጠላት እምቢ አልገዛም ባይነት ብቻ ሳይሆን እርስ በእርሰ መተባበርንና መከባበርን ጭምር ነው ብለዋል፡፡
የአገር መከላከያ ሰራዊት ከጀግኖች አርበኞች አገርን ከፈተና የመታደግ ጥበብን በመውረስ ይህንን በተግባር አሳይቷል ያሉት ደግሞ የመከላከያ ሰራዊትን ወክለው በክብረ በዓሉ ንግግር ያደረጉት ሜጀር ጀኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን ናቸው፡፡
የአገር መከላከያ ሰራዊት ጀግንነቱ በጦር ሜዳ ብቻ ሳይሆን በልማት ጭምር መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡