የመሪዎችን ንግግሮችና ያስተላለፏቸውን መልእክቶች ሰንዶ ማስቀመጥ የታሪክ ውዝግቦችን ለማስቀረት የላቀ ጠቀሜታ ይኖረዋል-የታሪክ ምሁር - ኢዜአ አማርኛ
የመሪዎችን ንግግሮችና ያስተላለፏቸውን መልእክቶች ሰንዶ ማስቀመጥ የታሪክ ውዝግቦችን ለማስቀረት የላቀ ጠቀሜታ ይኖረዋል-የታሪክ ምሁር
አዲስ አበባ ሚያዚያ 26/2015(ኢዜአ)፡ የመሪዎችን ንግግሮችና ያስተላለፏቸውን መልእክቶች ሰንዶ ማስቀመጥ የታሪክ ውዝግቦችን ለማስቀረት የላቀ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን የታሪክ ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ተናገሩ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አዘጋጅነት ቃል፣ ተግባር፣ ትውልድ በሚል በአብርሆት ቤተ መጻህፍት እየተካሄደ ያለው አውደ ርእይ እንደቀጠለ ነው።
በዛሬው እለትም "ከመጋቢት እስከ መስከረም" እና "ከመስከረም እስከ መስከረም" በሚል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛና እንግሊዘኛ ያደረጓቸውን ንግግሮችና ያስተላለፏቸውን መልክቶችን የያዙ መጽሃፍቶች ላይ ውይይት ተካሂዷል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው የመጽሃፍቶችን ይዘትና ጠቀሜታ በሚመለከት ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በገለፃቸውም በአለም ላይ የታላላቅ ሰዎችና መሪዎች ንግግሮች ተሰንደው የማግኘት ባህል መኖሩን አስታውሰዋል።
መሪዎች የሚያደርጓቸው ንግግሮች ህዝብን ለማስተባበር፣ አቅጣጫ ለማስያዝ፣ የመንግስትን የትኩረት አቅጣጫና አገር የምትሄድበትን የሚያሳዩ እንደሆኑም አመላክተዋል።
የመሪዎችን ንግግሮችና ያስተላለፏቸውን መልክቶች ሰንዶ ማስቀመጥ የታሪክ ውዝግቦችን ለማስቀረት የላቀ ጠቀሜታ አለው ነው ያሉት።
በመሆኑም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ መጽሃፍቶች፣ ንግግሮችና መልእክቶች ተሰንደው ለትውልድ መተላለፍ አለባቸው ብለዋል።
የመሪዎች ንግግሮችና ያስተላለፏቸውን መልእክቶች ሰንዶ መያዝ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው መሆኑንም አብራርተዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከፖሊሲ አቅጣጫና ለህዝብ ቃል የገቡትን ንግግሮች በማንሳት አፈጻጸማቸው ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም በኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ በማዕድን፣ በግብርና፣ በቱሪዝምና ሌሎች ዘርፎች የተዋቀረ የምጣኔ ሃብት አካሄድ ተተግብሮ በሁሉም የልማት ዘርፎች ውጤት መመዝገቡን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት በኮቪድ 19፣ በጦርነትና ሌሎችንም አለም አቀፍና የአገር ውስጥ ፈተናዎች ተቋቁሞ እድገት ማስመዝገብ መቻሉን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
መሰል መጽሃፎች መሪዎች በንግግራቸው የሚገቡትን ቃል ለመጠየቅና ግልጽነትን ለማስፈን ህዝብ የተገባለትን ቃል እንዲጠይቅ ያግዛል ተብሏል።
በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት አዘጋጅነት ለአንድ ሳምንት የሚቆየውና ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን የያዘው ቃል፣ ተግባር፣ ትውልድ በሚል በአብርሆት ቤተ መጻህፍት እየተካሄደ የሚገኘው አውደ ርዕይ ነገም የሚቀጥል ይሆናል።