ቀጥታ፡

ወደ መደበኛ ፖሊስ ለተቀላቀሉ የሲዳማ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ለነበሩ ሽኝት ተደረገ

ሀዋሳ  ሚያዚያ 26/2015 (ኢዜአ):- የሲዳማ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ለነበሩና ወደ መደበኛ ፖሊስ ለተቀላቀሉ ወደ ተመደቡበት ከተማ አስተዳደሮችና ወረዳዎች ዛሬ ሽኝት ተደረገላቸው።

የክልሉ ልዩ ኃይል አደረጃጀት በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ዕውቅና እንዳልነበረው የክልሉ የሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ጢሞቲዎስ በሽኝት ሥነሥርዓቱ ላይ ገልጸዋል፡፡


 

መንግሥት አንድ ወጥ ጠንካራ ህብረ ብሄራዊ የፀጥታ ኃይል ለማደራጀት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በክልል ደረጃ አስፈላጊውን ውይይት መደረጉን አስታውሰዋል።

ኃላፊው አክለውም ውይይቱን ተከትሎ በምርጫቸው ወደ መደበኛ ፖሊስ ለተቀላቀሉት ዛሬ ሽኝት ተደርጓል ብለዋል። 

አባላቱ በተመደቡበት አካባቢ ዜጎችን በቅንነትነ፣ በታማኝነትና በእኩልነት እንዲያገለግሉ አቶ ዓለማየሁ አሳስበዋል፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ሽመልስ ቶማስ በበኩላቸው የክልሉ ልዩ ኃይል የነበሩ አባላት በምርጫቸው የክልሉን መደበኛ ፖሊስ  እንዲቀላቀሉ የማድረጉ ስራና ምደባው ግልፅ አሰራርን መሰረት አድርጎ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡


 

አባላቱ ቀደም ሲል የክልሉን ህዝብ ሠላምና ደህንነት ለመጠበቅ በቁርጠኝነት ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ አሁንም ህዝብና መንግሥት የሰጣቸውን አደራ  በታማኝነት መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ወደ ተመደቡበት የከተማ አስተዳደሮችና ወረዳዎች ከተሸኙ አባላት መካከል ምክትል ሳጅን ዳኒሶ ዳሳ ወደ መደበኛ ፖሊስ ሲቀላቀሉ ያለምንም አስገዳጅ ሁኔታ በፍላጎታቸው  መሆኑን ተናግረዋል። 


 

ቀደም ሲልም መንግሥትና ህዝብ የሰጡንን ኃላፊነት በአግባቡ ስንወጣ ቆይተናል ያሉት ሳጅን ዳኒሶ በተመደቡበት አካባቢም ህዝብን በሙሉ ኃላፊነት  ለማገልገል ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።


 

ዋና ሳጅን በላይ ብርሃኑ በበኩላቸው የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት ከመንግሥት በተቀመጠው አቅጣጫ ላይ ከአመራሮች ጋር በመወያየት ውሳኔውን መቀበላቸውን ጠቅሰዋል።

ከዚህ በፊት ሀገር በፈለገችን ወቅት በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በግንባር ተሰልፈን ሀገራዊ ሠላም እንዲሰፍን ታግለናልም ብለዋል።

ዋና ሳጅን በላይ አክለውም ከዚህ በኋላም የህዝባችንን ሠላም ለመጠበቅ የሚጠበቅብንን ሁሉ እንወጣለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

በሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የከተማ አስተዳደሮችና የወረዳዎች አመራሮች ተገኝተዋል ፡፡

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም