ከሱዳን ተፈናቅለው በመተማ ዮሐንስ ከተማ ለተጠለሉ ወገኖች 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ከሱዳን ተፈናቅለው በመተማ ዮሐንስ ከተማ ለተጠለሉ ወገኖች 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ
መተማ ሚያዚያ 26/2015(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በሱዳን ባጋጠመው ችግር ሳቢያ ተፈናቅለው በመተማ ዮሐንስ ከተማ ለተጠለሉ ወገኖች 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ዛሬ አደረገ።
በማህበሩ የሰሜን ጎንደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አታለል ታረቀኝ እንዳሉት ድጋፉ የተደረገው በሱዳን ባጋጠመው ችግር ምክንያት ተፈናቅለው በመተማ ዮሐንስ ከተማ ለተጠለሉ 1000 ሰዎች ነው።
ድጋፉ ብርድ ልብስ፣ በፀሐይ ብርሃን የሚሰራ መብራት፣ ምንጣፍ፣ ሸራና የምግብ ማብሰያ ቁሳቁሶችን ያካተተ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኃላፊው አክለውም ድጋፉ የሱዳን ተፈናቃይ ወገኖችን ጊዜያዊ ችግራቸውን ለማቃለል የሚያስችል ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ከሌሎች ድጋፍ ሰጭ ተቋማት ጋር በመተባበር ቀደም ሲል 1 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረጉንም አስታውሰዋል።
ማህበሩ ካደረገው ምግብና ምግብ ነክ ካልሆኑ የቁሳቁስ ድጋፍ ባሻገር ከ560 በላይ ዜጎች የነፃ ስልክ አገልግሎት በመስጠት ከቤተሰቦቻቸው ጋር የማገናኘት ስራ መሰራቱንም ኃላፊው ተናግረዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል አቶ ዮሐንስ አብርሃም እንዳሉት ሁለት ህፃናት ልጆቻቸውን ይዘው ከሱዳን ካርቱም ወደ መተማ ዮሐንስ ከመጡ ሰባት ቀናት አልፏቸዋል።
አቶ ዮሐንስ አያይዘውም ከልጆቻቸው ጋር ባልተመቸ ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ ጠቅሰው፤ ዛሬ የተደረገላቸው ድጋፍ የዕለት ችግራቸውን የሚያቃልል መሆኑን ገልፀዋል።
"ዛሬ ላይ የተደረገልን ድጋፍ ምግብ አብስለን መብላትና መተኛት የሚያስችለን ነው" ያሉት ደግሞ አቶ ገብረመስቀል ፍፁም ናቸው።
አቶ ገብረመስቀል አያይዘውም እንደ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ሁሉ ሌሎች ረጅ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።