ኢትዮ ቴሌኮም አዳዲስ የዲጂታል መዝናኛ አገልግሎቶችን ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮ ቴሌኮም አዳዲስ የዲጂታል መዝናኛ አገልግሎቶችን ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 26/2015(ኢዜአ):- ኢትዮ ቴሌኮም ከአገልግሎት ሰጪ አጋሮቹ ጋር በመተባበር አራት አዳዲስ የዲጂታል መዝናኛ አገልግሎቶችን ዛሬ ይፋ አድርጓል።
በመጀመሪያው አገልግሎት በሐበሻ ቪው የሚቀርበው የቪዲዮ ስትሪሚንግ አንዱ ሲሆን፣ ደንበኞች የቀጥታ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን፣ድራማዎችን፣ፊልሞችንና ሌሎች የተመረጡ አገልግሎቶችን ኢንተርኔትን በመጠቀም በሞባይል ስልካቸው፣ በቴሌቪዥናቸው እንዲሁም በኮምፒውተር ላይ መመልከት እንደሚችሉ ገልጿል።
አገልግሎቱን ለአንድ ወር ያህል በነጻ ማግኘት እንደሚቻልና ከዛ በኋላ በወር ከ150 እስከ 300 ብር በመክፈል መጠቀም እንደሚቻል አመልክቷል።
በኢትዮ ቴሌኮም የቀረበው ሁለተኛው አገልግሎት የመዝናኛው ዘርፍ የዲጂታል አገልግሎት የሚሰጠው ሰዋሰው የሙዚቃ መተግበሪያ ሲሆን የአገር ውስጥና የውጪ ሙዚቃዎች በአንድ ቦታ የሚገኘቡትና የሚደመጡበት አማራጭ ነው።
አገልግሎቱንም በቴሌብር ሱፐርአፕ መተግበሪያና በሰዋሰው ድረ-ገጽ ላይ ማግኘት እንደሚቻል ገልጿል።
ዛሬ ይፋ የተደረጉት ሌሎች አገልግሎቶች ቴሌጌምና ቴሌዊን የተሰኙ የሞባይል ጌሞች ናቸው።
ጌሞቹ በቴክኖላብ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርና አይኮኔክት ዲጂታል ሰርቪስ የቀረቡ መሆናቸውን ኢትዮ ቴሌኮም ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ቴሌጌም አዋቂዎችም ሆኑ ታዳጊ ልጆች የተመረጡ 500 የሞባይል ጌሞችን በአነስተኛ ክፍያ ያለ ገደብ እንዲያወርዱና ያለ ጣልቃ ገብ ማስታወቂያዎች መጫወት እንደሚያስችላቸው አመልክቷል።
የጌም አገልግሎቱን ሁለት ቀን በነጻ መጠቀም እንደሚቻልና በቀን 3 ብር በመክፈል ደግሞ አገልግሎቱ እንደሚገኝ ነው ኩባንያው ያስታወቀው።
በተጨማሪም ደንበኞች በአይኮኔክት የቀረቡትን የቴሌዊን ጌሞችን በቴሌዊን ድረ-ገፅ ወይም በአጭር የፅሁፍ መልዕክት ወደ *985# በመደወል ዕለታዊ ወይም ሳምንታዊ ጥቅሎችን መመዝገብና መጫወት እንደሚችሉ ተገልጿል ።
ጌሞቹ በጥንቃቄ የተመረጡና ሁሉንም የእድሜ ክፍል ያማከሉ መሆናቸውን ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል።