በአባቶቻችን መስዋዕትነት የተረክብናትን ሀገር በአንድነት ሆነን ለቀጣይ ትውልድ እናወርሳለን" - የኦሮሚያ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ - ኢዜአ አማርኛ
በአባቶቻችን መስዋዕትነት የተረክብናትን ሀገር በአንድነት ሆነን ለቀጣይ ትውልድ እናወርሳለን" - የኦሮሚያ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ
መቱ ሚያዝያ 26/2015 (ኢዜአ) በአባቶቻችን መስዋዕትነት የተረክብናትን ሀገር በአንድነት ሆነን ለቀጣይ ትውልድ እናወርሳለን" ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሁሴን ፈይሶ ተናገሩ።
ኢትዮጵያውያን ከአድዋ ድል በኋላ የጣልያን ወራሪ ኃይል ድል ያደረጉበት በኢሉባቦር ዞን ጎሬ አካባቢ የሚገኘው የሳምቤ ሜዳ በኦሮሚያ እና በጋምቤላ ክልሎች አመራሮች ተጎብኝቷል።
በኢሉባቦር ዞን ጎሬ አካባቢ የሚገኘው የሳምቤ ሜዳ ኢትዮጵያውያን ከአድዋ ድል በኋላ ተደራጅቶ የመጣውን የጣልያን ወራሪ ኃይል ድል ያደረጉበት መሆኑን የቢሮ ሀላፊው አስታውስዋል።
"የዛሬው ትውልድም ኢትዮጵያውያን ከአድዋ ድል በኋላ ኃይሉን አጠናክሮ የመጣውን የጣልያን ወራሪ ሃይል ድል ባደረጉበት መንፈስ በመነሳሳት አገራዊ እድገትን በአንድነት ማረጋገጥ ይኖርብናል" ብለዋል።
"የዛሬው ትውልድ ሰላሟ የተጠበቀ፣ ዕድገቷ የተረጋገጠና ዜጎችን ተጠቃሚ የምታደርግ አገር ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ መትጋት አለብን" ሲሉም አክለዋል።
ኢትዮጵያውያን ወራሪውን ድል ያደረጉት ሀገራዊ አንድነታቸውን ጠብቀው በተባበረ ክንዳቸው መሆኑን ያስታወሱት አቶ ሁሴን፣ ድሉ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ነው በማለት ተናግረዋል።
የዛሬው ትውልድም በአባቶቻችን አንድነትና በብሔር ብሔረሰቦች የተባበረ ክንድ የተመዘገበውን ድል ለአገራዊ አንድነት ማጠናከሪያ ማዋል እንዳለበት ገልጸው፣ እንደ አገር የሚገጥሙ ፈተናዎችን በጋራ በማሸነፍ ለቀጣይ ትውልድ የበለፀገች ሀገርን ማስረከብ አለብን ብለዋል።