ዩኒቨርሲቲዎች ለኢንዱስትሪ ምርታማነት ማደግ ትልቅ ሚና ላላቸው የቴክኖሎጂና የፈጠራ ትምህርቶች በቂ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል-ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲዎች ለኢንዱስትሪ ምርታማነት ማደግ ትልቅ ሚና ላላቸው የቴክኖሎጂና የፈጠራ ትምህርቶች በቂ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል-ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 26/2015(ኢዜአ)፡-ዩኒቨርሲቲዎች ለኢንዱስትሪው ምርትና ምርታማነት ማደግ ትልቅ ሚና ላላቸው የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ትምህርቶች በቂ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ተናገሩ፡፡
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ "ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ለኢንዱስትሪ" በሚል መሪ ሃሳብ ለሁለት ቀናት የሚቆየውን 7ኛው ዓመታዊ የምርምር ጉባዔ ዛሬ ማካሄድ ጀምሯል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ምርምሮች ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት መጎልበት ሚናቸው ከፍተኛ ነው።
ተለዋዋጭ በሆነ ዓለም ተወዳዳሪ ሆኖ ለመራመድ የኢንዱስትሪ ዘርፉን በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ መደገፍ አከራካሪ ጉዳይ እንዳልሆነ አንስተዋል።
አትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ካስመዘገቡ ከሰሃራ በታች አገራት መካከል መሆኗን አስታውሰው፤ ይህን ዕድገት ለማስቀጠል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብቁ የሰው ኃብት ማፍራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
የግብርና፣ የጤና፣ የማዕድን እንዲሁም የማምረቻ እና ሌሎች የኢንዱስትሪ መስኮች ዕድገትን ለማረጋገጥ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በፈጠራ ትምህርቶች መደገፍ እንደሚገባ አመላክተዋል።
ሚኒስቴሩ ለተቋማት ተልዕኮ ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸው፤ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች በዘርፉ እያደረጉ ያሉትን ጥረት አድንቀዋል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ደረጀ እንግዳ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው በኢንዱስትሪ ችግር ፈቺ ምርምሮች እና በሰው ኃይል ልማት ውጤታማ ሥራዎች ማከናወኑን ጠቅሰዋል።
ዩኒቨርሲቲው በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመለየት የተለያዩ ምርምሮችን እያካሄደ መሆኑን ገልጸው፤ ጥናቶች ሲጠናቀቁ ለዘርፉ ምርትና ምርታማነት ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ ግኝቶችን እንደሚያመላክቱ ጠቁመዋል።
የዩኒቨርሲቲ እና የኢንዱስትሪ ትስስርን ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባር ተኮር ሥልጠናዎች ለተማሪዎች እየተሰጡ መሆኑንም ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የምርምር ጉባዔው ተሳታፊዎች ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማምጣት የኢንዱስትሪ ዘርፉን በዕውቀት መምራትና መደገፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተሞክሮዎችን አድንቀው፤ የኢንዱስትሪ ባለቤቶችም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በዘርፉ የሰለጠነ ብቁ የሰው ኃይል እንዲጠቀሙ ጠቁመዋል፡፡
ኮንፈረንሱ የእርስ በርስ መረጃዎችን ለመለዋወጥ እና በቀጣይ ተባብሮ ለመሥራት ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረውም እንዲሁ፡፡