በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች በስፋት የሚስተዋለውን የመጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መሥራት ይገባል-- ምክር ቤቱ - ኢዜአ አማርኛ
በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች በስፋት የሚስተዋለውን የመጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መሥራት ይገባል-- ምክር ቤቱ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 26/2015 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በስፋት የሚስተዋለውን የመጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መሥራት እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ16ኛ መደበኛ ስብሰባው የ15ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ-ጉባዔን መርምሮ በሙሉ ድምፅ ያጸደቀ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ማቋቋሚያ አዋጅ በቀረበው ረቂቅ ላይ በመወያየትም ለዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምፅ እንዲመራ ወስኗል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትም በዛሬው ውሎው ገምግሟል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሐብታሙ ኢተፋ፤ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ሪፖርቱን ለምክር ቤት አባላት አቅርበዋል።
በሪፖርታቸውም የብሔራዊ የውሃ ጥራት ቁጥጥርና ክትትል ሥርዓት ሽፋን ከነበረበት 15 በመቶ ወደ 24 በመቶ ማደጉን ገልጸዋል።
አገራዊ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ጥራትና ፍትሃዊ ተደራሽነትን ማረጋገጥን በተመለከተም 2 ሺህ 917 የመጠጥ ውሃ ተቋማት በመገንባት ከ1 ሚሊየን 867 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አመላክተዋል።
በተደጋጋሚ ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎችም ለመሥራት ከታቀዱት ዘጠኝ ፕሮጀክቶች አራቱን በማጠናቀቅ ከ110 ሺህ በላይ ዜጎችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የእንቦጭ አረምን ከውሃ አካላት ላይ ለማንሳት በተከናወኑ ሥራዎች 1 ሺህ 390 ሄክታር ቦታ ከአረሙ ማጽዳት መቻሉን ጠቁመዋል።
ለውሃ አካላት ተስማሚ የሆኑ ከ50 ሚሊየን በላይ ችግኞች ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ረገድም የኤሌክትሪክ ኃይል ምርት ከነበረበት 4 ሺህ 880 ሜጋ ዋት ወደ 5 ሺህ 420 ሜጋ ዋት ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭም 71 ነጥብ 17 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ አባላት የፕሮጀክቶች መጓተትና በሚፈለገው ፍጥነት ያለመሄድ ችግሮች መኖራቸውን በማንሳት፤ በሚኒስቴሩ የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች በይበልጥ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡
በንጹህ የመጠጥ ውሃ ተደራሽነት ላይ አሁንም መሰራት እንዳለበት እና አማራጮችን ማስፋት እንደሚገባ በማሳሰብ ከፍትሃዊነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጣቸው እንደሚገባም ነው የገለጹት።
ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሐብታሙ ኢተፋ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ የግብአት ዋጋ ንረት፣ የጸጥታ ችግር፣ የጥናትና ዲዛይን ሥራዎች በጥራት አለመሥራት ፕሮጀክቶች እንዲጓተቱ መንስኤ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በዚህም ዕቅዶችን በመከለስ የዋጋ ንረቱን ለማጣጣምና አማካሪዎች በተቀመጠላቸው መስፈርትና ጊዜ ሥራዎችን በጥራት በመሥራት እንዲያጠናቅቁ ለማስቻል እየተንቀሳቀስን ነው ብለዋል።
የግንባታ ዕቃዎች እጥረት ያለባቸውን ፕሮጀክቶች በመለየት ትስስር የመፍጠር ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሀ መስኖ፣ቆላማ አካባቢ እና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፈትያ አህመድ፤ የተቋሙ የሪፎርም ሥራዎች በጥንካሬ የሚነሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጠጥ ውሃን ተደራሽ ለማድረግ የሚሰሩ ሥራዎች ፍትሃዊነት በተሞላበት መልኩ ሊከናወኑ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በተደጋጋሚ ድርቅ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች የሚከናወኑ ሥራዎች ዘላቂ ልማትን የሚያረጋግጡ መሆን አለባቸው ብለዋል።
በውሃ አካላት ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረምን ለማጥፋት የተደረገው ጥረት በቂ ባለመሆኑ የሕዝብ ንቅናቄ በመፍጠር ቀጣይነት ያለው ሥራ ማከናወን ይገባል ብለዋል።