የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል-ሚኒስትር መላኩ አለበል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል-ሚኒስትር መላኩ አለበል
አዲስ አበባ ሚያዝያ 26/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ተናገሩ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ያዘጋጀው የ"ኢትዮጵያ ታምርት" የንቅናቄ መድረክ እና የኢንዱስትሪ ምርቶች አውደ ርዕይ ዛሬ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ሌሎች የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች እና አምራቾች ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ አምራቾች በዋናነት የመስሪያ ቦታ፣ የፋይናንስ፣ የኃይል አቅርቦት ፣ የገበያ ትስስር እና መሰል ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል መንግስት ለአምራች ኢንዱስትሪው ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት በመስራት የተለያዩ ማነቆዎችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን በመጥቀስ፤ አምራቾች የሚያነሷቸው ጥያቄዎችም ደረጃ በደረጃ እንደሚፈቱ አረጋገጠዋል።
መንግስት ለአምራች ኢንዱስትሪው የፖሊሲ ማዕቀፍ በማውጣት፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦትን ተደራሽ በማድረግ ሥራዎችን ማከናወኑንም ተናግረዋል።
በአገር ውስጥ ምርት መኩራት እና መጠቀም እንደሚገባ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ መንግስት ሁሉንም አቅሞች አሟጦ በመጠቀም ለአምራች ኢንዱስትሪው መጎልበት ይሰራል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅንቄም ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን በማንሳት በአዲስ አበባ የተከናወኑ ስራዎችም አበረታች ናቸው ብለዋል።
በቀጣይ በከተማዋ ያሉ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች በአቅማቸው ልክ በማምረት የሀገርን ኢኮኖሚ በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባት የበኩላቸውን እንዲወጡ አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ረገድ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለከተማዋ እና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በጋራ ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የኃይል አቅርቦት ችግር በሂደት እንደሚፈታ ጠቅሰው፤ የመስሪያ ቦታን በሚመለከት በከተማዋ ተጨማሪ 54 ሼዶች እየተገነቡ መሆኑን አመላክተዋል።
የፋይናንስ ችግሩን ለመፍታት ከቁጠባ እና ብድር ተቋማት እንዲሁም ከባንኮች ጋር በመተባበር መፍትሔ እንደሚሰጠው ጠቁመዋል።
አምራቾችም መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ በመጠቀም ለአገሪቱ ዕድገት የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅት እና ትብብር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።