ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል ግብርናን በማዘመን የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል ሁሉም ሊረባረብ ይገባል..ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ

ሀዋሳ ሚያዚያ 25 / 2015 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል የግብርና ሜካናይዜሽንን በማስፋፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተመዘገበው  አመርቂ ውጤት ቀጣይነት እንዲኖረው የክልሉ ህዝብ ርብርብ እንዲያደርግ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ  አስገነዘቡ።

የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተገኙበት 589 የእርሻ ትራክተሮች ርክክብ ሥነ-ሥርዓት ዛሬ በሻሸመኔ ከተማ ተካሂዷል።


 

በዚህ ወቅት  አቶ ሽመልስ እንዳሉት  በክልሉ  ከለውጡ ወዲህ በአዲስ እሳቤና ስትራቴጂ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ለማስመዝገብ በተደረገው ሁሉን አቀፍ ርብርብ ውጤት ተመዝግቧል።

በተለይ ሜካናይዜሽን እርሻን ለማስፋፋት፣ ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴን ስራ ለይ ለማዋልና የመስኖና የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በየደረጃው ለማስፋፋት በተደረገው ርብርብ አመርቂ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።

በተለይ በሰብል ልማት፣ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማትና የግብርና ሜካናይዜሽንን በማስፋፋት በተደረገው ያላሰለሰ ጥረት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሉን አውስተዋል።

''ክልሉ ካለው የተፈጥሮ ሀብት ጸጋና የሰው ሀብት አንፃር ያለውን አቅም ገና አሟጦ አልተጠቀምም'' ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣  በየደረጃው የሚገኙ አርሶና አርብቶ አደሮች፣ሴቶችና ወጣቶች መንግሥት የቀየሰውን በቤተሰብ ደረጃ ብልጽግና ለማረጋገጥ ለተያዘው ግብ መሳካት እንዲረባረቡ አሳስበዋል።

ይህንን ይበልጥ ለማጎልበት በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት የሚተገበር አዲስ እቅድ የክልሉ መንግሥት መንደፉን ገልጸው፣ ለእቅዱ ስኬት መላው የክልሉ ህዝብ እንዲረባረብ አስገንዝበዋል። 

ምንም እንኳን አየር ንብረት ለውጡ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ህብረተሰቡን ለችግር እያጋለጠ ቢሆንም፤ በተሰራው ጠንካራ ስራ የከፋ ችግር እንዳላጋጠመ አመልክተዋል።

ይህንን ተጽእኖ ለመቋቋም እንዲቻልና ምርትና ምርታማነትን በብዛትና በጥራት ለማሳደግ እንዲቻል የግብርና ልማቱን በማዘመን በመጪው መኸር እርሻ ወቅት 80 በመቶ የሚሆነውን መሬት በኩታ ገጠም ለመሸፈን ይሰራል ብለዋል።

ከክልሉ መንግሥት የትኩረት መስኮች መካከል የኢኮኖሚ አቅም መገንባት መሆኑን የገለፁት ደግሞ  የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አወሉ አብዲ ናቸው።


 

እስካሁን በተደረገው ጥረት ከዚህ በፊት በክልሉ ያልተለመዱ የፍራፍሬ ልማትን ጨምሮ ኢኮኖሚን የሚያሳድጉ ስራዎችን በማከናወን በቤተሰብ ደረጃ ብልጽግና ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

በአርሶ አደሮችና በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች የእርሻ ትራክተር ተጠቃሚ በማድረግ ሰፊ ልማት ውስጥ እየተገባ እንደሚገኝ አውስተዋል።

የትራክተሩ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል የቦረና ዞን ያቤሎ ወረዳ አርሶ አደር ጃተኒ ታሪ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም በአርብቶ አደሩ አካባቢ የእርሻ ልማት እምብዛም እንደነበር ጠቅሰው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ባመቻቸላቸው እድል በመጠቀም ልማት ውስጥ መግባታቸውን ተናግረዋል።

በአከባቢያቸው ላይ ትራክተር በመከራየት በዓመት ከ35 እስከ 50 ሄክታር መሬት ላይ ጤፍ፣ ስንዴና ቦለቄ እንደሚያለሙ ገልጸው ባገኙት ትራክተር ሰፊ መሬት በማልማት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ከጉጂ ዞን መልካሶዳ ወረዳ ሰለሞን ከበበ እንደሚለው መንግሥት አርሶ አደሩን የትራክተር ተጠቃሚ እንዲሆን ያመቻቸውን እድል ለመጠቀም 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በመቆጠብ 120 የፈረስ ጉልበት ያለውን ትራክተር ለመረከብ መቻሉን አውስቷል።

ባለፉት ዓመታት የእራሻ ትራክተር በኪራይ በመጠቀም ያለኝን ልምድ በማጎልበት የሰብል ልማቱን በማስፋፋት ለሌሎችም ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር መነሳሳት እንደፈጠረለት ተናግሯል።

እስካሁን ከአንድ ጓደኛው ጋር በዓመት በ200 ሄክታር መሬት ላይ የስንዴ ልማት ሲያካሂዱ እንደነበር ጠቁሞ የግል ትራክተር ባለቤት በመሆናችን የምናለማውን መሬት በቀጣይ 500 ሄክታር ለማድረስ አቅደናል ብለዋል። 

አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች የእርሻ ትራክተሮቹን እየተረከቡ ያሉት የትራክተሩን ዋጋ 30 በመቶ በመቆጠብ ቀሪው 70 በመቶው ክፍያ ደግሞ በመንግሥት የባንክ ብድር ተመቻችቶላቸው ነው።

ለሥራ ፈላጊ ወጣቶች ደግሞ የትራክተሩን ዋጋ 90 በመቶ መንግሥት ከባንኮች ጋር በማስተሳሰር ብድር ማመቻቸቱን ጠቁመው፣ ቀሪውን 10 በመቶ ወጣቶች በቁጠባ መክፈል እንደሚጠበቅባቸው ተመላከቷል።

ተጠቃሚዎቹ በዘመናዊ ግብርና ልማት እንቅስቃሴ በመሰማራት በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ብድራቸውን ከፍለው የትራክተር ባለቤት ይሆናሉ።

ለአርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች እንዲሁም በማህበር ለተደራጁ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች እየተከፋፈሉ ያሉት የእርሻ ትራክተሮች በኬኛ የግብርና መሳሪያዎች ማምረቻ ድርጅት ተገጣጥመው የተመረቱ  ናቸው።

በእርሻ ትራክተሮቹ የርክክብ ሥነ-ሥርዓት ላይ የክልሉ ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ ሌሎች የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ አባ-ገዳዎች፣ ሀደ ስንቄዎች፣ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም