ቀጥታ፡

ጉምሩክ ኮሚሽን የተለያዩ ተቋማት ጋር የአንድ መስኮት የኤሌክትሮኒክ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 26/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ከተለያዩ ተቋማት ጋር የአንድ መስኮት የኤሌክትሮኒክ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።

ኮሚሽኑ የተፈራረመው ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን እና ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር ነው። 


 

ከስምምነቱ በኋላ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ፤ ኮሚሽኑ አሠራሩን በቴክኖሎጂ ታግዞ በማዘመን ውጤታማ ሥራዎች ማከናወኑን ገልጸዋል።

በዛሬው እለት የተደረገው የአንድ ማዕከል ኤሌክትሮኒክ አገልግሎት ስምምነትም አሠራሩን ይበልጥ ቀልጣፋና ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችለው መሆኑን ተናግረዋል።

የንግድ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግና የደንበኞችን እርካታ ለመጨመር እንዲሁም ሙስናን ለመከላከልም የላቀ ፋይዳ አለው ብለዋል።


 

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አዲሱ ማሞ፤ ከኮሚሽኑ ጋር የተደረገው ስምምነት ለተቋማቸው የላቀ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

የአንድ መስኮት ኤሌክትሮኒክ አገልግሎት የወጪና ገቢ ሥራዎችን በተቀላጠፈ መልኩ ለመስጠት ወሳኝ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ፤ ለሕዝብ የሚሰጠውን አገልግሎት የተቀላጠፈ ለማድረግ ከኮሚሽኑ ጋር የአንድ መስኮት አገልግሎት ስምምነት መፈረሙ የላቀ ትርጉም አለው ብለዋል።

በኮሚሽኑ በኩል ተቋማቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ በመሆኑም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ተወካይ ሙላይ ወልዱ፤ ጉምሩክ ኮሚሽን ከብዙ ተቋማት ጋር ግንኙነት ያለው እንደመሆኑ እንደዚህ ዓይነት እርምጃዎች ሥራዎቻቸውን ለማቃለል ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ የአንድ መስኮት ኤሌክትሮኒክ አገልግሎት ፕሮግራም ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ሮቤል ተስፋዬ፤ የኤሌክትሮኒክ አንድ መስኮት አገልግሎት ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ለአስመጪና ላኪዎች፣ ለኢንቨስትመንትና ለንግዱ ማኅበረሰብ ሥራን ቀልጣፋ ለማድረግና አገልግሎትን ለማፋጠን ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም