መገናኛ ብዙኃን ከምንም በላይ ለአገር ሰላም፣ ልማትና አንድነት በልዩ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙኃን ከምንም በላይ ለአገር ሰላም፣ ልማትና አንድነት በልዩ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 26/2015(ኢዜአ)፡- መገናኛ ብዙኃን የአገርና ሕዝብን ጥቅም በማስቀደም ትክክለኛ መረጃ ተደራሽ በማድረግ ለሰላም፣ ልማትና አንድነት በልዩ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ።
ናሽናል ሚዲያ /ኤን ቢ ሲ ኢትዮጵያ/ የቴሌቪዝን ጣቢያ በይፋ ሥራ ጀምሯል።
የጣቢያውን ምስረታ በማስመልከት በተዘጋጀው መርሃ-ግብር የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ አንጋፋ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች፣ አርቲስቶችና ታዋቂ ግለሰቦች እንዲሁም የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ተገኝተዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃብት ቢሮ ኃላፊ ሂክማ ካይረዲን፤ ዜጎች በሁሉም መስኩ ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኙ በማድረግ ሂደት የመገናኛ ብዙኃን ቁልፍ ሚና ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የሕዝብን ሰላምና አንድነት ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ አንዳንድ የሚዲያ ተቋማት መኖራቸውን ጠቅሰው፤ መገናኛ ብዙኃን የአገርና ሕዝብን ጥቅም በማስቀደም ትክክለኛ መረጃ ተደራሽ በማድረግ ለሰላም፣ ልማትና አንድነት በልዩ ትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም ናሽናል ሚዲያ ለሕዝብ ትክክለኛ መረጃ በማድረስና በአገር ገጽታ ግንባታ ሂደት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ጋር በተናበበ መልኩ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይኸው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አማረ አረጋዊ፤ በኢትዮጵያ አሁን ላይ እየገጠሙ ያሉ ችግሮች መፍትሔ ማበጀት ላይ ከመገናኛ ብዙኃን ብዙ ይጠበቃል ብለዋል።
በተለይም ሐሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ትርክቶችን ለመቀልበስ መገናኛ ብዙኃን ብዙ መሥራት አለባቸው ነው ያሉት።
በዚህ ረገድ ናሽናል ሚዲያ የድርሻውን ሚና ይጫወታል የሚል እምነት አለኝ ሲሉም ተናግረዋል።
የናሽናል ሚዲያ አክሲዮን ማህበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ከበደ፤ መገናኛ ብዙኃን በአንድ አገር ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና እድገት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
ለዚህም ናሽናል ሚዲያ /ኤን ቢ ሲ ኢትዮጵያ/ የቴሌቪዝን ጣቢያ የድርሻውን ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የቴሌቪዥን ጣቢያውን ለማቋቋም በግንባታ፣ ለሥርጭት የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችን በ500 ሚሊዮን ብር በማሟላት ለሁለት ዓመት ዝግጅት መደረጉን አስታውሰዋል።