ቀጥታ፡

​​​​​​​በኢትዮጵያ የዳበረ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንካራ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል-  የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት 

አዲስ አበባ ሚያዚያ 26/2015 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ የዳበረ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግን የተከተለ ጠንካራ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ አለሙ ገለጹ።

በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ሁሉንም አሳታፊ ያደረገ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመፍጠር በመንግሥት በኩል ሰፊ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑ ይታወቃል።

ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት አሳሪ የነበሩ ሕጎችን በማሻሻል፣ በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራጅተው በሃሳብ የበላይነት አሸናፊ የሚሆኑበት አሠራርም ተዘርግቷል።

በዚህ ሂደት በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎች የነቃ ተሳትፎና የመነጋገር ባህል መዳበር ወሳኝ መሆኑን በርካቶች ይናገራሉ።


 

ከዚሁ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ አለሙ፤ በአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የተሳካ እንዲሆን በተለይም የፓርቲዎች ሚና የላቀ መሆኑን ይናገራሉ።

በአንድ አገር የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት በፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ የሃሳብ የበላይነትን መነሻ ያደረገ የክርክር ልምድ መዳበር እንዳለበት ገልጸዋል።

የሃሳብ ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅም ተግባር መፈጸም የሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ኃላፊነት መሆን አለበት ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የአገርንና የሕዝብን ጥቅም የማስቀደምና የማስጠበቅ ግዴታ አለባቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የዳበረ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግን የተከተለ ጠንካራ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባልም ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማምጣት ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ መሥራት እንዳለባቸውም ዶክተር መብራቱ ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም