የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ተጨማሪ እድሎችን ይዘው መጥተዋል- አስጎብኚ ድርጅቶች - ኢዜአ አማርኛ
የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ተጨማሪ እድሎችን ይዘው መጥተዋል- አስጎብኚ ድርጅቶች

አዲስ አበባ ሚያዚያ 26/2015 (ኢዜአ):- የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ተጨማሪ እድሎችን ይዘው መምጣታቸውን አስጎብኚ ድርጅቶች ተናገሩ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሀሳብ አመንጪነት በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ጎርጎራ፣ ወንጪ እና ኮይሻ ላይ የቱሪዝም ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰሞኑ የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነውን ሐላላ ኬላ ሪዞርት መርቀው መክፈታቸውም ይታወቃል።
ይህን ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው አስጎብኚ ድርጅቶች፤ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ተጨማሪ እድሎችን ይዘው መምጣታቸውን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቶቹ በአዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራ፣ በስራ እድል ፈጠራ እና በውጭ ምንዛሬ ግኝት ያላቸው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ገልፀዋል።
የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የጎብኚዎች የቆይታ ጊዜ እንዲራዘም በማድረግ በኩል ትልቅ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
የአማን ኢትዮጵያ አስጎብኚ እና የጉዞ ወኪል ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አማኑኤል አሰፋ፤ ፕሮጀክቶቹ ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ ጎብኚዎች ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከመፍጠራቸው ባለፈ የገቢ አቅምን የማሳደግ እድሎችን ፈጥረዋል ነው ያሉት።
የአድማሱ ትራቭል ኤንድ ቱርስ መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ አድማሱ ገበየሁ በበኩላቸው፤ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የጎብኚዎች የቆይታ ቀናትን በማራዘም በሆቴል፣ በትራንስፖርት እና በአስጎብኚ ዘርፍ የተሰማሩ አካላት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲጎለብት አስቻይ ሁኔታዎችን እየፈጠሩ ነው ብለዋል።
ከለውጡ ወዲህ ከፖሊሲ ማዕቀፍ እስከ ትግበራ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች የቱሪዝም ዘርፉ የበለጠ እንዲነቃቃ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዘርፉ የሚከናወኑ ተግባራት በዚህ ከቀጠሉ በጥቂት ጊዜ ኢትዮጵያ በዓለም ካሉ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ቀዳሚዋ እንደምትሆን ያላቸውን እምነት አጋርተዋል።
የኦሮሚያ ቱር ኦፕሬተር አሶሴሽን ፕሬዚዳንትና የቱሀይላይት ቱር ኤንድ ትራቭል ኤጀንት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ይታየው ታሪኩ፤ የገበታ ለሀገር ሜጋ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ ከዘርፉ ተጠቃሚነቷን ለማጎልበት የሰጠችውን ትኩረት እንደሚያሳይ ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቶቹ ኢትዮጵያን ከዚህ ቀደም የጎበኙ ቱሪስቶች ዳግም እንዲመጡ ለማድረግ ተጨማሪ አቅምና ጉልበት የሚፈጥሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አሸናፊ ካሳ በበኩላቸው፤ በገበታ ለሀገር የተሰሩ ፕሮጀክቶች ዘመናዊነትን የተላበሱ ለየት ያለ ዘውግ ያላቸው መሆኑን ገልጸው ለቱሪዝም ዘርፉ ተጨማሪ አማራጮችን ያጎናጸፉ ናቸው ብለዋል።
እነዚህን የቱሪዝም አቅሞች የበለጠ ለመጠቀምና ለተቀረው ዓለም ለማስተዋወቅ ህብረተሰቡ በቱሪዝም ላይ ያለው ግንዛቤ እንዲዳብር መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ የገበታ ለሀገር ሜጋ ፕሮጀክቶችን ለውጭ ጎብኚዎች በማስተዋወቅ ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝቷ እንዲጨምር ለማድረግ እንደሚሰሩም ጭምር ነው የተናገሩት።