የጀርመን መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስ በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ - ኢዜአ አማርኛ
የጀርመን መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስ በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 26/2015 (ኢዜአ) የጀርመን መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስ በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ አዲስ አበባ እንደሚገቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በሳምንታዊ መግለጫቸው፤ የጀርመን መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ የንግድ እና የሚዲያ ልዑካን ቡድንን ይዘው ዛሬ አዲስ አበባ እንደሚገቡ ተናግረዋል።
መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
የኢትዮጵያን እና የጀርመንን የረጅም ዘመን ግንኙነት ወደ ላቀ ምዕራፍ ማሸጋገር የሚያስችሉ ውይይቶች እንደሚኖሩም ነው ቃል አቀባዩ የጠቀሱት።
ከመሪው ጋር የሚመጡ የጀርመን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት በሚሰማሩበት ሁኔታ እና የንግድ ትስስርን ለማጎልበት ምክክር እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች ተከታታይ ጉብኝት ኢትዮጵያ ከአውሮፓ አባል ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት ከመጠራጠር ወደ መተባበር የተለወጠ መሆኑን የሚሳይ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው ብለዋል።
አምባሳደር መለስ የኢትዮጵያ የድሕረ ጦርነት የዲፕሎማሲ ዘርፍ መነቃቃት ማሳየቱን ገልፀው፣ በቀጣይ ሳምንት የማልታ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡም ጨምረው ገልጸዋል።