በሱዳን በተፈጠረው ችግር ሳቢያ 61 ሀገሮች ዜጎቻቸውን በኢትዮጵያ በኩል እንዲያስወጡ መንግስት ድጋፍና ትብብር አድርጓል-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በሱዳን በተፈጠረው ችግር ሳቢያ 61 ሀገሮች ዜጎቻቸውን በኢትዮጵያ በኩል እንዲያስወጡ መንግስት ድጋፍና ትብብር አድርጓል-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ሚያዚያ 26/2015(ኢዜአ)፦ በሱዳን በተፈጠረው ችግር ሳቢያ 61 ሀገሮች ዜጎቻቸውን በኢትዮጵያ በኩል እንዲያስወጡ መንግስት ድጋፍና ትብብር ማድረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በሳምንታዊ መግለጫቸው፤ ሱዳን እና ኢትዮጵያ በመልክዓ ምድር፤ በህዝብ ለህዝብና በኢኮኖሚ የተሳሰሩ ሀገሮች በመሆናቸው፣ በሱዳን የተፈጠረው የሚያሳስበን እና በትኩረት እየተከታተልነው ያለ ጉዳይ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ችግሩ በሱዳናውያን እውቀት እና ጥበብ በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ በውይይት እንዲፈታ እንደምትሻ ገልፀዋል።
በጎረቤት ሱዳን የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ 61 ሀገሮች ዜጎቻቸውን በኢትዮጵያ በኩል እንዲያስወጡ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ማድረጉንም ተናግረዋል።
እስካሁንም ለ75 የበረራ አገልግሎቶች ፈቃድ መሰጠቱን ገልፀው፣ ይህ ትብብርም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ መርህን የተከተለ እና ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጎልበት የሚያግዝ ነው ብለዋል።
እስካሁንም ከ7 ሺህ 700 በላይ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ገልጸው፤ ከእነዚህም መካከል 3 ሺህ 517ቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው።
በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ደኅንነት በማረጋገጥ እና ክትትል በማድረግ በኩል በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲን ጨምሮ ብሔራዊ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በታሪኳም የተቸገሩ ዜጎች መጠለያ መሆኗን ገልጸው፤ ችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ባላት ውስን ሀብት ተቀብላ እያተስተናገደች መሆኑን ገልጸዋል።