ቀጥታ፡

የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የጎላ ሚና አለው -- ምሁራን

ሀዋሳ ሚያዚያ 26/2015 (ኢዜአ):-ዘንድሮ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች መስጠት የሚጀመረው የተመራቂ ተማሪዎች መውጫ ፈተና እንደ ሀገር በትምህርቱ ዘርፍ ጥራት ለማረጋገጥ የጎላ ሚና ይጫወታል ሲሉ ምሁራን ተናገሩ ፡፡ 

የዩኒቨርሲቲ መግቢያና መውጫ ፈተና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ባለው አስተዋጽኦ ላይ ያተኮረ ሀገራዊ የምርምርና ጥናት ጉባኤ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡


 

በጉባኤው ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን በፈተናው አሰጣጥና እንደ ሀገር ባለው ጠቀሜታ ዙሪያ መነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡

ከጽሁፍ አቅራቢዎቹ መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር በላይ ሀጎስ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ከትምህርት ጥራት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡

በተለይ ተማሪዎች ሳይዘናጉ ሙሉ ጊዜያቸውን በማንበብ እንዲሁም ንቁ ሆነው እንዲዘጋጁ ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡

የመውጫ ፈተና በትምህርት ዘርፍ ጥራትን ለማረጋገጥና በተቋማት ግንባታ ሂደት ውስጥ ብቁና ንቁ የሰው ኃይል እንዲኖር በማድረግ የሚጫወተው ሚና የጎላ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

ሌላው ጽሁፍ አቅራቢ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የኢንግሊዘኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር መብራቱ ሙላቱ የመውጫ ፈተና ወስደው የሚመረቁ ተማሪዎች በአብዛኛው ተቋማትን ይቀላቀላሉ ይላሉ፡፡

በተቋማት ውስጥ ብቃት ያላቸው ዜጎች ካሉ አፈፃፀማቸው የተሻለ እንደሚሆን ጠቅሰው ይህም በሀገር ዕድገት ላይ የሚኖረው አበርክቶ የጎላ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የመውጫ ፈተናውን አልፈው የሚወጡ ምሩቃን በሀገር ውስጥ ብቻም ሳይሆን ዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሊያደርጋቸው የሚችል ብቃት ይዘው እንደሚወጡ ነው የገለጹት፡፡

አሁንም ቢሆን ተማሪዎችን ለመውጫ ፈተና በስነ ልቦና ዝግጁ ከማድረግ አኳያ የግንዛቤ ማስጨበጫና ሌሎች ሥራዎች በተጠናከረ መልኩ መሰራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡


 

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ በበኩላቸው የመውጫ ፈተናው በርትተው የሚሰሩና ብቁ የሆኑ ምሩቃን ብቻ አልፈው ወደ ሰው ኃይል ገበያው እንዲቀላቀሉ በማድረግ ለታታሪዎች መልካም ዕድልን የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡

ዘንድሮ በዩኒቨርሲቲው ከ3 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና እንደሚወስዱም ገልፀዋል፡፡

''ሁሉም ተማሪዎች በብቃት ፈተናውን እንዲያልፉ ዕቅድ ይዘን እየሰራን ነው'' ያሉት ፕሬዚዳንቱ ለፈተናው በቂ ዝግጅት ከማድረግ አኳያ ለተማሪዎች፣ ለመምህራንና ለአስተዳደር አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሰራቱን ጠቅሰዋል፡፡

ለተማሪዎች የክለሳና የማጠናከሪያ ትምህርት እንደሚሠጣቸው ገልጸው ሞዴል ፈተናዎችም እየተዘጋጁላቸው እንደሆነ አስረድተዋል ፡፡

በጥናትና ምርም ጉባኤው ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን፣ የአስተዳደር አካላትና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ተገኝተዋል፡፡


 


 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም