በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከ15 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ አዳዲስ መንገዶች እና የጥገና ስራ ተከናውኗል - የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከ15 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ አዳዲስ መንገዶች እና የጥገና ስራ ተከናውኗል - የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር
አዲስ አበባ ሚያዝያ 25/2015 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በ2015 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ከ15 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ አዳዲስ መንገዶች እና የነባር መንገዶች ጥገና ስራ ማከናወኑን አስታወቀ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ቋሚ ኮሚቴ የአስተዳደሩን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸምን ዛሬ ገምግሟል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሀመድ አብዱራህማን ኢንጂነር መሀመድ በዘጠኝ ወራቱ ካለፈው ዓመት ወደ ዘንድሮ የተሸጋገሩና አዳዲስ የተጀመሩ 23 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ርዝመት ያላቸው 322 የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።
በዘጠኝ ወራት ውስጥ 6 ሺ 300 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ መከናወኑን አመልክተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ አስተዳደሩ 11 ሺህ ኪሎ ሜትር የጥገና ስራዎችን ለማከናወን አቅዶ 9 ሺህ ኪሎ ሜትር ወይም የዕቅዱን 83 ከመቶ ማሳካቱን ተናግረዋል።
አዲስ ለተጀመሩና በሂደት ላይ ላሉ ፕሮጀክቶች ከመንግስት፣ከልማት አጋሮችና ከመንገድ ፈንድ 69 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ዓመታዊ በጀት ተመድቦ እየተሰራ መሆኑን ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያብራሩት።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ፣ ጥራት እና ወጪ እንዲጠናቀቁ በቅርብ ክትትልና ድጋፍ የሚያደርጉ 27 የግንባታ ፕሮጀክት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤቶች ማቋቋሙን አመልክተዋል።
ከነዚህም ውስጥ 25ቱ ስራ መጀመራቸውን የጠቀሱት ኢንጂነር መሐመድ ጽሕፈት ቤቶቹ ፕሮጀክቶችን በቅርበት ለመከታተል፣ ለመቆጣጠር እና የፕሮጀክት አመራር ሥርዓትን እያጠናከሩ ነው ብለዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ የሚስተዋሉ መጓተቶችን ለመቅረፍ በትኩረት እንዲሰራ ጠይቀዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ፤ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ፕሮጀክቶችን በቅርብ የሚከታተልና የሚደግፍ መዋቅር በአጭር ጊዜ ለማቋቋም የሄደበት ርቀት መልካም የሚባል ነው ብለዋል።
ሁሉም የፕሮጀክት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በሙሉ አቅም ወደ ስራ ገብተው የተቋቋሙበትን ዓላማ እንዲያሳኩ አስተዳደሩ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
በመንገዶች ቅድመ ግንባታና በግንባታ ወቅት የወሰን ማስከበር እና የካሳ ክፍያ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑን በቋሚ ኮሚቴው የመስክ ምልከታ ማረጋገጥ መቻሉን ነው ሰብሳቢዋ ያመለከቱት።
የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች መዘግየት መንግስትን ለከፍተኛ ወጪ እየዳረገው በመሆኑ ከሌሎች የመሠረተ ልማት ተቋማት ጋር በቅንጅት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
ከካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥመውን ችግር ለመፍታትም የሕግ ማዕቀፎች እንዲጸድቁ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በቀጣይ ጥረት ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።
አስተዳደሩ ሕዝቡ ከሚያነሳው የመንገድ ጥያቄ አንጻር በበጀት ዓመቱ ቀሪ ጊዜያት ለመፈጸም የታቀዱ ፕሮጀክቶችን ለማሳካት በልዩ ትኩረት እንዲሰራም ወይዘሮ ሸዊት አሳስበዋል።