ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የያዘውን ከፍታና የመሪነት ሚና ለማስቀጠል ከኤር ባስ ኩባንያ ጋር ግንኙነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 25/ 2015 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የያዘውን ከፍታና የመሪነት ሚና ለማስቀጠል ከኤር ባስ  ኩባንያ ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ  አቶ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 20ኛውን ኤር ባስ A350-900 አውሮፕላን ባሳለፍነው ሳምንት መረከቡ ይታወሳል።

አየር መንገዱ በአውሮፕላኑ የተጓጓዘውን 10 ቶን የሚመዝን የሰብአዊ ድጋፍ ቁሳቁስ ለተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ዛሬ አስረክቧል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው እንዳሉት፤አየር መንገዱ ከእ.አ.አ 2016 ጀምሮ ከኤር ባስ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ጋር የቢዝነስ አጋርነት መስርቷል።

በዚህ ሂደት ቀደም ብሎ ከኤር ባስ ኩባንያ ካዘዛቸው 24 አውሮፕላኖች መካከል 19ኙን መረከቡንና ባለፈው ሳምንት 20ኛውን የኤር ባስ አውሮፕላን መረከቡን አስታውሰዋል።

አዲሱ  ኤር ባስ A350-900 የመንገደኞች አውሮፕላን ''አድዋ'' የተሰኘ ስያሜ እንደተሰጠው የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው አውሮፕላኑ ነዳጅ ቆጣቢና ምቹ መሆኑን አመልክተዋል።

ይህም ዓለም አቀፉ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ እ.ኤ.አ. በ2050 የካርቦን ልቀትን ዜሮ ለማድረስ የያዘውን ውጥን ከግብ ለማድረስ እንደሚረዳም ገልጸዋል።

አየር መንገዱ በአፍሪካ የያዘውን ከፍታና የመሪነት ሚና ለማጠናከር ከኩባንያው ጋር  የቢዝነስ አጋርነቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል አቶ መስፍን።  

በተያያዘም በመጪው መስከረም ወር ከቦይንግ ኩባንያ ሌሎች ተጨማሪ አውሮፕላኖችን እንደሚያስገባ ጠቁመው ይህም የአየር መንገዱን የጉዞ መዳረሻ እንደሚያሳድገው ተናግረዋል፡፡

የኤር ባስ ኩባንያ የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ  ሀገራት ዓለም አቀፍ የንግድ ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ሃንዲ አኮውም፤ የካበተ ልምድና ስመጥር ከሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ያለን አጋርነት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።


 

 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ 144 አውሮፕላኖችና ከ140 በላይ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች እንዳሉት ገልጿል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም