ቀጥታ፡

ለኢንተርፕራይዞች ከዋስትና ነፃ የብድር አገልግሎትን በስፋት ማዳረስ የሚያስችል የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 25/2015 (ኢዜአ) ለጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ከዋስትና ነፃ የብድር አገልግሎትን በስፋት ማዳረስ የሚያስችል የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ተገለጸ።

የክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ከዋስትና ነፃ የብድር አገልግሎት የሚመቻችበት ሁኔታ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል።

የክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙኒር ዱሪ፤ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የተሰማሩ ዜጎች ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርሱ የፋይናንስ አቅርቦት የሚያስፈልጋቸው መሆኑን በመድረኩ ላይ አንስተዋል።

በመሆኑም ለጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ከዋስትና ነፃ የብድር አገልግሎት ተደራሽነትን ማመቻቸት ይገባል ብለዋል።

ከዋስትና ነፃ የብድር አገልግሎት የሚሰጠው በዘርፉ የተሰማሩ ዜጎችን መረጃዎች በዲጅታል ምዝገባ በማካሄድና ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በማቆራኘት የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም በዘርፉ በተለይም የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓትን በማስፋት ለፋይናንስ ፈላጊ ኢንተርፕራይዞች ብድር የማቅረብ ስርአት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ፤ የብድር ሥርዓቱን ቀልጣፋ፣ ዘመናዊና ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል የአሠራር ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የፋይናንስ አገልግሎትን ቀልጣፋና ዘመናዊ ለማድረግ የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓትን መተግበር ይገባል ብለዋል።

ለዚህም መንግሥት የተንቀሳቃሽ ንብረት ዋስትና ሥርዓትን ከመዘርጋት ጎን ለጎን ዋስትና የሌላቸው ተበዳሪዎች የሚስተናገዱበት አሠራር መዘርጋቱን ጠቅሰዋል።

በሁሉም ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት ተግባራዊ እንዲሆን ለማስቻልና ቅንጅታዊ አሠራሩ ይበልጥ እንዲዳብር ባንኩ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም