አገር በቀል ዕውቀቶች ለዘላቂ ሰላም ግንባታና አብሮነት

1542

በጣፋጩ ሰለሞን

 አገራችን ኢትዮጵያ የተለያየ ቋንቋ፣ ባህልና እምነት ያላቸው በርካታ ብሄር፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ተቻችለው፣ ተከባብረው፣ ተዋደው፣ በአንድነትና በአብሮነት በፍቅር የሚኖርባት አገር ነች።

በዚህም የብሄር ብሄረሰቦች ሙዝዬም ነች የሚል አድናቆትን ተጎናፅፋለች-ኢትዮጵያ። እነዚህ ብሄር፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የራሰቸው መገለጫ የሆኑ ቱባ ባህል አላቸው።

ኢትዮጵያውያን ለዘመኑ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ጥበብ መሰረት የሆኑ የአያሌ  አገር በቀል ዕውቀቶች ባለቤቶች ናቸው። ባህላዊ የመድኃኒት ቅመማና የህክምና ጥበብ ኢትዮጵያ ለዓለም ካበረከተቻቸው ትሩፋቶች መካከል አገር በቀል ዕውቀቶች ተጠቃሽ እንደሆኑ የታሪክ ድርሳናትና ሌሎች የየዘርፉ ተጓዳኝ መረጃዎች ያስረዳሉ።

በተለይ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የተጠቀሙባቸውና እየተጠቀሙባቸው ያሉ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ለሌሎችም ጭምር በአርዓያነት የሚጠቀሱ  ናቸው።

 በጂንካ ዩኒቨርስቲ 5ኛው አገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ ሰሞኑን ተካሂዷል።

በኮንፈረንሱ በአገር በቀል ግጭት አፈታት ዘዴዎች ለዘላቂ ሰላም፣ለአብሮነት ትስስር እና ለአገራዊ ዕድገት ያላቸው ሚና የሚል እሳቤን ዓላማ ያደረገ  ጥናት ቀርቧል።

ጥናቱ .. 2018 እስከ 2022 ባሉ ዓመታት በመስቃን እና በማረቆ ህዝቦች ባህላዊ የግጭት አፈታት ላይ መሰረት አድርጎ የተካሄደ ነው።

ጥናቱን ያካሄዱት "አገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች ለሰላም፣ ለፀጥታ እና ለዕድገት ያላቸው አስተዋፅኦ፤The Role  of Indigenous conflict resolution Mechanism for peace,Security ,and Sustainable Development in Ethiopia " በሚል ርዕስ ያካሄዱት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርና ተመራማሪ ዮሐንስ ተስፋዬ ናቸው።

የጥናቱ ግኝት እንደሚያመለክተው ዘመናትን ተሻግረው እዚህ የደረሱ የሰላም ግንባታና ማጠናከሪያ የሆኑ አገር በቀል ዕውቀቶች አሁን ለደረስንበት ሳይንሳዊ ጥበብ መጎልበት  እያገለገሉ  ነው።

የጥናት አቅራቢው ለኮንፈረንሱ ታዳሚዎች እንዳብራሩት ጥናቱ አገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ለአብሮነትና ለዕድገት አይተኬ ሚና አላቸው።

እነዚህን አገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች በአግባቡ መጠቀም ይገባል።

እሳቸው እንዳብራሩት በአገራችን ሶስት አይነት የግጭት አፈታት ዘዴዎችን እንጠቀማለን። የወንጀልና የፍትሐብሔር ህጎች፣ እንደ ሽምግልና ያሉ አገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች እና ከሃይማኖታዊው ደግሞ ሸርዓ ከምንጠቀምባቸው የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው።

ተመራማሪ ዮሐንስ እንዳሉት ጥናቱ በተካሄደበት በጉራጌ ዞን በመስቃን እና በማረቆ መካከል አጋጥሞ የነበረውን አለመግባባት ከመፍታት አኳያ ከዘመናዊ እውቀቶች ይልቅ አገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች ትልቅ ሚና ነበራቸው።

በመስቃን እና በማረቆ ያጋጠመውን አለመግባባት ለመፍታት ከመስቃን፤ ከማረቆ እንዲሁም ከአጎራባች የኦሮሚያና ስልጤ ዞኖች የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣  አባ ገዳዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል።

በመስቃን እና በማረቆ መካከል  ያጋጠመውን አለመግባባት ለመፍታት የተሳተፉት የሀይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች ግጭቱን ለመፍታት የተጠቀሙት ጥበብ አገር በቀል ዕውቀቶች በዘመናዊ ህግና አሰራር የማይቻሉትን የመፈጸምና ማህበራዊ አንድነትን ከማጠናከር አንፃር ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው የጥናቱ ግኝት አመላክቷል። አለመግባባቱን ለመፍታት 26 ዙር  ለመሸምገል ተቀምጠዋል።

 በማሸማገሉ ሂደት የተሳተፉት የሃይማኖት አባቶች፣  አባ ገዳዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሁለቱን ማህበረሰቦች ለማቀራረብና በአካባቢው እረቀ-ሰላም ለማወርድ የከፈሉት መስዋዕትነት ቀላል አለመሆኑን በአጽኖኦት አስረድተዋል።

የትኛውንም ውጣ ውረድና ጫና ተቋቁመው ሳይታክቱ ችግሩን የፈቱበት መንገድ ለዘመናዊው አስተዳደር ትምህርት የሚሰጥና በቅርስነት ለትውልድ የሚተላለፍ ሰናይ ተግባር መሆኑንም አስረድተዋል።

ግጭቶች ቀደም ሲል የነበሩ፣ አሁንም ያሉና ወደፊትም የሚኖሩ ናቸው። በተለያዩ ምክንያቶች የሚያጋጥሙ ግጭቶችን ፖለቲካዊ ትርጉም በመስጠት ከማጦዝ ይልቅ አገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ተጠቅሞ ለማርገብ መስራት አዋጭና ተመራጭ መንገድ መሆኑን የጥናቱን ግኝት ዋቢ አድርገው ተመራማሪ ዮሐንስ መክረዋል።

ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ለአገር በቀል እውቀቶች ተገቢውን ዕውቅና መስጠት ይገባል። አገር በቀል ዕውቀቶችን በትምህርት ሥርዓት ውስጥ አካቶ ለማጎልበት የተጀመረው አበረታች ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመላክተዋል።

 አገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች ከቂም በቀል በፀዳ መልኩ አብሮነትን ለማጠናከር እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው ያሉት ደግሞ የጂንካ ዩኒቨርስቲ የባህል ተመራማሪና የዩኒቨርስቲው የምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ኤሊያስ ዓለሙ ናቸው።

አክለውም ዘመናዊ ሕግን ተከትሎ በሚሰጡ ብያኔዎች አንዱ ወገን የሚደሰትበት ሌላኛው ደግሞ ቅር ተሰኝቶ የሚከፋበት ናቸው ይላሉ።

በማህበራዊ ሸንጎ ግን ሁለቱም ወገን የሚደሰቱበት፣ ከልብ ይቅር ተባብለው ችግሮቻቸውን የሚፈቱበትና ዘላቂ እርቀ-ሰላም የሚያወርዱበት እንደሆነም ያስረዳሉ።

ዶክተር ኤሊያስ አክለውም ይህም ማህበራዊ አንድነት ለማጠናከር ፋይዳው የላቀ ነው። የሚያጋጥሙ አለመግባባቶችን  ለመፍታትና በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በአገራችን ቱባ ባህሎች ውስጥ ያሉ አገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎችን መጠቀም ይገባል።

በባህላዊ እሴቶቻችን ውስጥ ያሉ አገር በቀል ዕውቀቶች ቀጣይነት ባለው መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውሉና ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆኑ ዕውቅና መስጠት፣ በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ማካተት፣ በአግባቡ አደራጅቶና ሰንዶ ለትውልድ ማስቀመጥ እንደሚገባ አመላክተዋል። ለዚህ ደግሞ ምሁራን የሚጠበቅብንን ኃላፊነት በአግባቡ ልንወጣ ይገባል ይላሉ።

አቶ መምህሩ ገዙሜ በጂንካ ዩኒቨርስቲ በሶሻል አንትሮፖሎጂ የትምህርት ክፍል የሶሽዮሎጂ መምህር ናቸው። አገር በቀል ዕውቀቶች ለአገራዊ ችግሮቻችን መፍቻ መንገዶች ናቸው ይላሉ። የሳይንሳዊ ምርምሮች ፅንሰ-ሀሳብ መነሻው አገር በቀል ዕውቀቶች እንደሆኑ ይጠቅሳሉ። በአገራችን በርካታ አገር በቀል ዕውቀቶች ቢኖሩም እንዳለመታደል በአግባቡ መጠቀም አልቻልንም ሲሉም ያክላሉ።

እሳቸው እንዳሉት መንግሥት አሁን ለአገር በቀል ዕውቀቶች የሰጠው ዕውቅና ለአገር በቀል ዕውቀቶች መጎልበትና ጥቅም ላይ መዋል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።

ይህን ዕድል በመጠቀም አገር በቀል እውቀቶች ጎልተው እንዲወጡና በትምህርት ሥርዓቱ ተካተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ መስራት ይገባል።

በተለይ የማህበረሰቡ የግጭት አፈታት ዘዴና በምክክር ችግሮችን የመፍታት ጥበብ የታሰበው አገራዊ የምክክር መድረክ ውጤታማ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

በመሆኑ አገር በቀል ዕውቀቶች ለዘላቂ ሰላም ግንባታ፣ ለኢትዮጵያውያን የአብሮነት ትስስርና መስተጋብር መጠንከር እንዲሁም ለአገር ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልፅግና እጅግ የላቀ ድርሻ ያላቸው መሆኑን ተገንዝቦ ተገቢውን ዕውቅና በመስጠት መጠቀም ይገባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም