በአገሪቱ ሰላምን የማፅናት እና የመልሶ ማቋቋም ስራዎችን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
በአገሪቱ ሰላምን የማፅናት እና የመልሶ ማቋቋም ስራዎችን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ ሚያዚያ 25/2015(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ሰላምን የማፅናት እና የመልሶ ማቋቋም ስራዎችን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ህብረት ልማት ኤጀንሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ ናርዶስ በቀለ ጋር ተወያይተዋል።
በኔፓድ የልማት መርሃግብሮች አተገባበር እና የሀገራት ሚና ላይ ያተኮረው ውይይት ላይ አቶ ደመቀ መኮንን እንደገለፁት የኔፓድ የልማት መርሃግብሮች በአፍሪካ ድህነትን ለመቀነስ እየተደረገ ላለው ጥረት ጉልህ እገዛ አለው።
ለልማት መርሃግብሮቹ ተፈፃሚነት ኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶም አቶ ደመቀ ለዋና ስራ አስፈጻሚዋ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን ሰላምን የማፅናት እና የመልሶ ማቋቋም ስራዎችን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።
ኔፓድ በአህጉሪቱ የሚያከናውናቸውን የልማት ተግባራት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
የአፍሪካ ልማት ኤጀንሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ ናርዶስ በቀለ በበኩላቸው የኔፓድ መርሃግብሮች የአፍሪካ የህብረት አጀንዳ 2063 በሚል ለያዛቸው የእድገት እቅዶች መሳካት ወሳኝ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
ኔፓድ የወጠናቸውን እቅዶች ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ያሉ የፋይናንስ ጉድለቶችን ለመሙላት የሃብት ማሰባሰብ ስራ አስፈላጊ መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ገልፀዋል።
ኔፓድ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው የልማት ትብብር በግብርና፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ፣ በአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርኘራይዞች እንዲሁም መሰል የልማት መስኮች በትብብር እንደሚሰሩ በውይይቱ ተገልጿል።