ቀጥታ፡

ከምእራብ ጉጂ ዞን ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ

ነገሌ ሚያዝያ 25 / 2015 (ኢዜአ):- ከምእራብ ጉጂ ዞን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የዞኑ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

ለግድቡ ግንባታ ከዞኑ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለመሰብሰብ ከሚያዝያ 19 እስከ ግንቦት 10 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ የቦንድ ሽያጭ መርሀ ግብር በቡሌ ሆራ ከተማ ተጀምሯል፡፡

በጽህፈት ቤቱ የሚዲያና የመረጃ ባለሙያዎች ቡድን መሪ አቶ ተመስገን ባቲ እንደገለጹት፤ የቦንድ ሽያጩ ቡሌ ሆራና ቀርጫ ከተሞችን ጨምሮ በዞኑ 11 ወረዳዎች ይካሄዳል፡፡

በህዳሴ ግድብ ድጋፍና ትብብሩ የዞኑን ሴቶችና ወጣቶችን ጨምሮ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ አመልክተው፤ እስካሁን ከተካሄደው የቦንድ ሽያጭ 4 ሚሊዮን 762 ሺህ ብር መሰብሰቡንና ቃል መገባቱን ገልጸዋል፡፡

በገቢ ማሰባሰብ ሂደቱ የዞኑ ሴቶችና ወጣቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ጎልቶ እየታየ እንደሆነ ገልጸው፤ የግድብ ግንባታ ላይ የታየው ስኬት የዞኑን ህዝብ ለድጋፍና ትብብር ማነሳሳቱን አመልክተዋል።

የዞኑ ህዝብ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰው፤ ባለፉት 8 ወራት ለግድቡ ግንባታ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ መሰብሰቡን ጠቁመዋል፡፡

በዞኑ ለወጣቶች ቦንድ ለመሸጥ ከታቀደው  4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር  ውስጥ  እስካሁን   2 ሚሊዮን 441 ሺህ ብር መሸጡን  የዞኑ ወጣቶች ሊግ ሀላፊ ወጣት ጌቱ ኔንቆ  አስታውቋል፡፡

በዞኑ ወጣቶች የተጀመረው ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝቧል።

የ15 ሺህ ብር ቦንድ የገዛው የቀርጫ ከተማ ነዋሪ ወጣት ተስፋዬ አሬሪ፤ ግድቡ ከኛም አልፎ ለአፍሪካዊያን ወገኖቻችን ጭምር የኤሌክትሪክ ሀይል በማመንጨት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ታላቅ ፕሮጀክት ነው ብሏል፡፡

የግድቡን ግንባታ ኢትዮጵያዊያን ተባብረን በእልህና በቁጭት እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን ብሏል፡፡

የዚሁ ከተማ ነዋሪና የ10 ሺህ ብር ቦንድ የገዛው ወጣት ሮባ አኖሌ፤ የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ የጀመረውን ተሳትፎ እንደሚያስቀጥል ገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም