በኦሮሚያ ክልል ያለውን ግጭት በማስወገድ ሰላምን ለማምጣት በታንዛኒያ ሲካሄድ የቆየው የሰላም ውይይት የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ያለውን ግጭት በማስወገድ ሰላምን ለማምጣት በታንዛኒያ ሲካሄድ የቆየው የሰላም ውይይት የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 25/ 2015 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ያለውን ግጭት በማስወገድ ሰላምን ለማምጣት ያለመውና በታንዛኒያ ሲካሄድ የቆየው የሰላም ውይይት የመጀመሪያ ምዕራፍ ዛሬ መጠናቀቁን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ያወጣው ሙሉ መግለጫ የሚከተለው ነው፦
በኦሮሚያ ክልል ያለውን ግጭት በማስወገድ ሰላምን ለማምጣት ያለመውና በታንዛኒያ ሲካሄድ የቆየው የሰላም ውይይት የመጀመሪያ ምዕራፍ ዛሬ ተጠናቋል።
ውይይቱ በአብዛኛው በአዎንታዊ መልኩ የተከናወነ ቢሆንም በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ግን በዚህኛው የውይይት ምዕራፍ ስምምነት ላይ ለመድረስ አልተቻለም። ግጭቱን በዘላቂነትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማስቆም እንዲቻል ሁለቱም አካላት የሰላም ውይይቱን መቀጠል አስፈላጊ መሆኑ ላይ ተግባብተዋል።
በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትና እስካሁን ሲመራባቸው በነበሩ መሠረታዊ መርሖች መሠረት ግጭቱን በሰላማዊ መልኩ ለመፍታት መንግስት የጸና አቋም አለው። ይህንን መልካም አጋጣሚና በውይይት ችግሮችን የመፍታት በጎ ጅምር በመጠቀም ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ የኢትዮጵያ መንግሥት ያለውን ፅኑ አቋም ዳግም ያረጋግጣል።
የሰላም ውይይቱን ላመቻቹና ላስተናገዱ አካላት የኢፌዴሪ መንግሥት ምስጋናውን ያቀርባል።