የህይወት ዋጋ እየከፈለ የኢትዮጵያ መከታ የሆነውን የአገር መከላከያ ሰራዊት በሀሰተኛ መረጃ ለመከፋፈል የሚጥሩ አካላት ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል-የቀድሞ ጦር ሠራዊት አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
የህይወት ዋጋ እየከፈለ የኢትዮጵያ መከታ የሆነውን የአገር መከላከያ ሰራዊት በሀሰተኛ መረጃ ለመከፋፈል የሚጥሩ አካላት ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል-የቀድሞ ጦር ሠራዊት አመራሮች
አዲስ አበባ ሚያዚያ 25/2015(ኢዜአ)፡- የህይወት ዋጋ እየከፈለ የኢትዮጵያ መከታ የሆነውን የአገር መከላከያ ሰራዊት በሀሰተኛ መረጃ ለመከፋፈል የሚጥሩ አካላት ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል ሲሉ የቀድሞ ጦር ሰራዊት አመራሮች ገለጹ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት አመራሮች ሻለቃ ታመነ አባተ እና ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ፤ የአገር መከላከያ ሠራዊት የህዝብ አለኝታና የአገር መከታ በመሆኑ የሁላችንም ክብር ይገባዋል ይላሉ።
በተለይም አሁን ላይ ሕብረ ብሔራዊ በሆነ መንገድ ተደራጅቶ፣ በቴክኖሎጂና በትጥቅ ዘምኖ ጠንካራ ሰራዊት በመገንባቱ የአገር ኩራት መሆኑን ገልጸዋል።
የአሁኑ ሠራዊት ከቀድሞው ጦር በተሻለ መንገድ የተደራጀ፣ ዘመናዊ መሳሪያዎችን የታጠቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሀገር ፍቅር ስሜትና ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት የህይወት ዋጋ የመክፈል ዝግጁነት ያለው ሰራዊት መሆኑንም ተመልክተናል ብለዋል።
ከኢትዮጵያ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰላም ማስከበር ያሳያቸው ትላልቅ ገድሎች እና ወታደራዊ ዲሲፕሊን የኢትዮጵያን ሠራዊት ታማኝነትና የሚያኮራ መሆኑን የሚያረጋግጥ መሆኑን ሻለቃ ታመነ አባተ ገልጸዋል።
የትኛውንም ጠላት በአስተማማኝ መልኩ በመመከት የሀገርን ዳር ድንበር እና የህዝብን ሰላም ማስጠበቅ የሚያስችለው ቁመና ላይ በመሆኑ ለሁላችንም ክብር ሆኗል ብለዋል።
ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ሠራዊት ከጥንት ጀምሮ ትጥቁ ልብ መሆኑን ገልጸው፤ ጀግንነት እና አሸናፊነት መለያው ነው ብለዋል።
ሠራዊቱ ከየትኛውም አካባቢ እና ማህበረሰብ ቢወጣም ወደ መከላከያ ሲገባ እንደ አዲስ በኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ ነው የሚቀረጸው ብለዋል።
መከላከያ ሠራዊት ከኢትዮጵያ ህዝብ አብራክ የወጣ የሀገር መከታ መሆኑን አንስተው፤ "የሠራዊቱ ቀዳሚ የኩራቱ ምንጭ እና አለኝ የሚለው ሀብቱ የኢትዮጵያ ሠራዊትነቱ እና የሀገር ፍቅር ነው" ብለዋል።
ህዝብ እና ሀገር ትልቅ የደህንነት መተማመኛቸው መከላከያ ሠራዊቱ እንደሆነ የተናገሩት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፤ ሠራዊቱ የኢትዮጵያ የመጨረሻው ምሽግ መሆኑን ገልጸዋል።
ሰራዊቱ በዘመናዊ አደረጃጀትና ትጥቆች የተሟላ መሆኑና ለሀገር የትኛውንም ዋጋ ለመክፈል የተዘጋጀ በመሆኑ አድናቆት የሚቸረው ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሠራዊት ከጥንት ጀምሮ ከመሳሪያው ጀርባ ኢትዮጵያዊ ወኔን የታጠቀ በመሆኑ በማንም የማይሸነፍ የጀግኖች ስብስብ መሆኑንም አስታውሰዋል።
አንዳንድ ከውጭ አካላት ተልዕኮ የተቀበሉ አካላት ሠራዊቱን ለመከፋፈል እየጣሩ መሆኑን ታዝበናል ያሉት የቀድሞ ጦር መኮንኖቹ እኩይ አላማቸው ሊሳካ የማይችል መሆኑን ገልጸዋል።
የአገር መከላከያ ሰራዊት ከየትኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ በመሆኑ ለየትኛውም ሀሰተኛ መረጃ ሸብረክ የማይል መሆኑን በተግባር እያሳየ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የህይወት ዋጋ እየከፈለ የኢትዮጵያ መከታ የሆነውን የአገር መከላከያ ሰራዊት በሀሰተኛ መረጃ ለመከፋፈል የሚጥሩ አካላት ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል ነው ያሉት።
የአገር መከላከያ ሰራዊትን መንካት ሀገርን ለማፍረስ መሞከር በመሆኑ ህዝቡ የጥፋት ሃይሎችን ሴራ በማክሸፍ ከሰራዊቱ ጎን እንዲቆምም ጠይቀዋል።