በኢትዮጵያ የጃዝ ሙዚቃ ተቀባይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል - የጃዝ ሙዚቀኞች - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የጃዝ ሙዚቃ ተቀባይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል - የጃዝ ሙዚቀኞች
አዲስ አበባ ሚያዚያ 25/2015(ኢዜአ)፡-በዓለም ላይ ትልቅ ተቀባይነት ያለው የጃዝ ሙዚቃ በኢትዮጵያም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል ሲሉ የጃዝ ሙዚቀኞች ተናገሩ።
ጃዝ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ከአፍሪካ ወደ አሜሪካ በመጡ ጥቁር የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች እንደመነጨ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ።
አፍሪካዊያኑ በምሽት ክበቦች ውስጥ ጃዝን አዘውትረው መጫወታቸው የሙዚቃ ስልቱ ይበልጥ ተደማጭነትና ተቀባይነት እንዲያገኝ አስችሏል።
ይህንንም ተከትሎ ስልቱ በዓለም ዙሪያ እየተስፋፋ እንዲሁም በየጊዜው አዲስ የሙዚቃ አቅጣጫዎችን እየያዘ አሁን ላይ ትልቅ የሙዚቃ ዘውግ ሆኗል።
አንጋፋው ኢትዮጵያዊ ሙዚቀኛ ሙላቱ አስታጥቄ ጃዝን ከባህላዊ የሙዚቃ ሥልቶች ጋር በማዋሃድ በኢትዮጵያ ይበልጥ ለማስተዋወቅ ችሏል።
የጃዝ ሙዚቃ ተጨዋችና መምህር የሆነው ኤልያስ ሙሉጌታ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለውን የጃዝ ሙዚቃ እንዲያድግ በተለያዩ ቦታዎች መድረኮች መዘጋጀት እንዳለባቸው ይገልፃል።
የሙዚቃ ሥልቱም በኢትዮጵያ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገት እያሳየ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ነው የገለፀው።
ሌላኛው የጃዝ ሙዚቀኛና መምህር እሱባለው አዳሙ በበኩሉ፤ የጃዝ ሙዚቃ መድረኮች መስፋፋት ሰዎች ስለ ኢትዮ-ጃዝ ግንዛቤ እንዲያገኙና እርስ በርስ ተገናኝተው ሙዚቃ እንዲያደምጡ ያደርጋል ብሏል።
የጃዝ ሙዚቃ እንዲስፋፋም ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣና ሙዚቀኛውም የጃዝ ሥራውን ለገንዘብ ሳይሆን ለሙያው ፍቅር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መልዕክቱን አስተላልፏል።
የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበራት ዘርፍ ፕሬዝዳንት ሙዚቀኛ ዳዊት ይፍሩ የጃዝ ሙዚቃ እንዲስፋፋና እንዲያድግ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ አለበት ብሏል።
ይህንንም ተከትሎ ከመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ጋር ውይይት መደረጉን ጠቁመው በቀጣይም ውይይቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና መፍትሄ እንደሚፈላለግ ነው የገለጸው።
የዓለም የጃዝ ቀን እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በየዓመቱ ሚያዝያ 30 ቀን የሚከበር ሲሆን፤ ዘንድሮም በኢትዮጵያ ለ12ኛ ጊዜ ከጀርመን ኤምባሲ ስኩል ጋር በመተባበር ተከናውኗል።