ቀጥታ፡

የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 25/2015(ኢዜአ)፦ በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት መርሐግብር የሶስተኛ ቀን ውሎ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ይደረጋሉ።

መቻል ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ መቻል በ26 ነጥብ 11ኛ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ በ27 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

መቻል በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። አራት ጊዜ ተሸንፏል።

ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ በሶስቱ ተሸንፏል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

በሌላኛው የ22ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐግብር ኢትዮ ኤሌትሪክ ከኢትዮጵያ መድን ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ኢትዮ ኤሌትሪክ በ11 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ኢትዮጵያ መድን በ38 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ኢትዮጵያ ኤሌትሪክ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።

ሁለት ጊዜ ተሸንፏል፤ ሶስት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። 

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል።

ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን 2 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል።

ከዛሬ ጨዋታዎች በኋላ የውድድሩ የአዳማ ቆይታ እንደሚጠናቀቅ የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።

ቅዳሜ ሚያዚያ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ከሚካሄዱ ሁለት የ22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ 27ኛ ሳምንት ያለው መርሐግብር በሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም እንደሚካሄዱ ገልጿል።

በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የ22ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች  ባህር ዳር ከተማ ከአርባ ምንጭ ከተማ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ከአዳማ ከተማ በተመሳሳይ ሁለት አቻ ተለያይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም