ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እያስመዘገበች ያለው ውጤት በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት ሁነኛ ማሳያ ነው- የዛምቢያ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ሚኒስትር

አዲስ አበባ ሚያዝያ 24/2015(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እያስመዘገበች ያለው ውጤት በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት ሁነኛ ማሳያ መሆኑን የዛምቢያ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ሚኒስትር ኤልያስ ሙባንጋ ተናገሩ።

የኒጀር፣ ታንዛኒያ፣ ዛምቢያና ኮትዲቩዋር ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች የልዑካን ቡድን የተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎችን ለመጎብኘት ከቀናት በፊት አዲስ አበባ መግባቱ ይታወቃል።


 

የልዑካን ቡድኑ እስካሁን በኦሮሚያ ክልል በግብርና ዘርፍ የተከናወኑ የልማት እንቅስቃሴዎችን ጎብኝቷል።

የልዑካን ቡድኑ አባላት በምስራቅ ሸዋ ዞን የበጋ ስንዴ እና የአቮካዶ ልማት ክንውኖችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ ኢዜአ ያነጋገራችው የዛምቢያ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ሚኒስቴር ኤልያስ ሙባንጋ፤ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እያከናወነቻቸው ያሉ የልማት ስራዎች አስድናቂ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

በሰብል ምርት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ሌሎች መስኮች የላቀ ውጤት የታየባቸውን የልማት ስራዎች አይተናል ብለዋል።

በመሆኑም በግብርናው ዘርፍ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለው ውጤት በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት ሁነኛ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌሎች የአፍሪከ ሀገራትም ኢትዮጵያ በስንዴና በአቩካዶ ልማት ላይ ያሳየችውን ስኬታማ ስራ በተሞክሮነት በመውሰድ ማልማት አለባቸው ብለዋል።


 

የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን በሕብረት ስራ ማህበር ተደራጅተው ራሳቸውን ከመለወጥ አልፈው ለሌሎችም ዜጐች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን አድንቀዋል።

በአብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት ወጣቶች ምሩቃን ስራ ፈላጊዎች እንጂ ስራ ሲፈጥሩ አይስተዋልም ያሉት ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ወጣቶች ተሞክሮ ለዛምቢያ ጥሩ ልምድ የሚሆን ነው ብለዋል።


 

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኅላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በ2011 ዓ.ም በየተጀመረው የበጋ መስኖ ልማት አሁናዊ የመሬት ሽፋኑ ከባለፈው ዓመት ዕጥፍ በማሳደግ ወደ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።

በተያዘው የ2015 የበጋ መስኖ 38 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልፀው፤ በተለይም በክላስተር እርሻ የግብርና ስርዓት በመተግበር ውጤታማ ለማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

ጉብኝቱ በፓን አፍሪካዊነት መንፈስ ወንድማማችነትን ለማጠናከር እና አፍሪካ ከድህነት ለመውጣት ለምታደርገው ጥረት ሀገራት በየዘርፉ የተሻለ ተሞክሮ ለመለዋወጥ እንደሚያግዝም ገልፀዋል።


 

በክልሉ ግብርና ቢሮ የቡና እና የአትክልትፋ ፍራፍሬ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኅላፊ አቶ መሃመድ ሳኒ በበኩላችው የክልሉ አቮካዶ ልማት ከሀገር ውስጥ ገበያ ባሻገር ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሉንና ለሀገር ኢኮኖሚዊ ዕድገት ተስፋ የተጣለበት መሆኑን ገልጸዋል።

በ2012 ጀምሮ እስካሁን ወደ 60 ቶን በላይ የአቮካዶ ምርት ለገበያ መቅረቡን ጠቅሰው፤ በአቮከዶ ልማት 43 ሺህ አርሶ አደሮች በቀጥታ ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል።


 

በዘንድሮው ዓመት 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአቮካዶ ችግኞች በክልሉ በ100 የአቮካዶ ችግኝ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸው ለመትከል የክላስተር መሬት ልየታ እና የጉድጓድ ቁፋሮ ተጠናቋል ብለዋል።

በክልሉ በቀጣይ ሶስት ዓመታት 40 ሺህ ሄክታር መሬት በአቮካዶ ለመሸፈን ታቅዷል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም