የሸገር ከተማ አስተዳደር በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤናና በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ትኩረት አድርጎ ለመስራት መዘጋጀቱን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የሸገር ከተማ አስተዳደር በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤናና በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ትኩረት አድርጎ ለመስራት መዘጋጀቱን ገለጸ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 24/2015 (ኢዜአ) የሸገር ከተማ አስተዳደር በቀሪዎቹ የበጀት ዓመቱ ወራትና ቀጣይ በጀት ዓመት በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤናና በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ትኩረት አድርጎ ለመስራት መዘጋጀቱን ገለጸ።
የሸገር ከተማ አስተዳደር የባለፉት ዘጠኝ ወራት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ ማጠቃላይ መርሃ-ግብር ተከናውኗል።
በዚሁ ወቅት የከተማው ከንቲባ ዶክተር ተሾመ አዱኛ፤ ሸገር ከተማ በበጀት ዓመቱ በተለያዩ ዘርፎች በተከናወኑ ስራዎች የተሻለ ውጤት መስመዝገቡን ተናግረዋል።
በተለይም በግብርና ልማት መስክ ሰፋፊ ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸው በመስኖ ልማትና በእንስሳት እርባታ የተሻለ ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል።
ከፕሮጀክቶች አፈጻጸምም አንጻር በከተማ አስተዳደሩ የተሰራው ሥራ አበረታች መሆኑን በግምገማ ለማወቅ እንደተቻለም አንስተዋል።
ይሁን እንጂ የልማት ሥራዎች አፈጻጸሙ አሁንም በክፍለ ከተሞች ደረጃ ሲታይ በተወሰነ ልዩነት እንዳለው ገልጸዋል።
በእቅድ አፈጻጸም ግምገማው ከተማ አስተዳደሩ በቀሪዎቹ የበጀት ዓመቱ ወራትና በቀጣይ በጀት ዓመት በግብርና፣ በከተማ ልማት፣ በመንገድ፣ በትምህርትና በጤና ዘርፍ በተለየ ሁኔታ ለመስራት መግባባት ላይ ተደርሷል ሲሉም ዶክተር ተሾመ ገልጸዋል።
በተጠቀሱት ዘርፎች ውጤታማ ሥራ ለመስራት እንዲቻል ከከዚህ በፊቱ በተለየ ሁኔታ መስራት እንደሚገባም የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም ገልጸዋል።
በተለይም በግብርና ዘርፍ ዘንድሮ ከታረሰው 60ሺህ ሄክታር መሬት በተጨማሪ 75 ሺህ ሄክታር መሬት ለመጨመር ታቅዷል ነው ያሉት።
ከዚህም ባለፈ በትምህርትና በጤና ዘርፍ ተደራሽነትንና ጥራትን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራም ከንቲባው ጠቅሰዋል።
በከተማው የአገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን ከመልካም አስተዳደር ጋር የሚያያዙ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የአንድ ማዕክል የዲጂታል አገልግሎት ለመስጠት ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ከንቲባው ጠቁመው፣ ይህም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይዞ ይመጣል ሲሉ ገልጸዋል።