ቀጥታ፡

ሕገ ወጥ የመድኃኒትና የምግብ ንግድ ዝውውርን ለመከላከል የመገናኛ ብዙሃን መረጃ ተደራሽ የማድረግ ሚና ወሳኝ ነው- የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን

ሀዋሳ፣ ሚያዚያ 24 /2015 (ኢዜአ):- ሕገ ወጥ የመድኃኒትና የምግብ ንግድ ዝውውርን ለመከላከል የመገናኛ ብዙሃን መረጃ ተደራሽ ማድረግ ጉልህ ሚና እንዳለው የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር መቅረፍ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከመገናኛ ብዙሃን አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር በሻሸመኔ ከተማ እየመከረ ነው።

የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ ዘንድሮ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀው የማቋቋሚያ ደንብ የባለስልጣኑ ተግባርና ኃላፊነት ምርት ተኮር እንዲሆን በማድረጉ ለስራ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።

ተቋማዊ የለውጥ ስራው የሕግ ማዕቀፎችን ለማሻሻል፣አደረጃጀትን ተደራሽ ለማድረግ፣ የአሰራር ስርዓትንና መሠረተ ልማትን በተገቢው ለመዘርጋት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ባለስልጣኑ በቀጣዮቹ አስር ዓመታት ባለስልጣኑ በዘርፉ በአፍሪካ ደረጃ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ ዘርፉ ከሰው ሕይወት ጋር የሚገናኝ በመሆኑ ተሻጋሪና ቀጣይነት ያለው የቁጥጥር ስራ መስራት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

ሕገ ወጥ የመድሃኒትና ምግብ ንግድ ዝውውርን ለመከላከል ሕብረተሰቡን የቁጥጥሩ ባለቤት ማድረግና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት ወሳኝ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

ከዚህ አንጻር ከቁጥጥርና ክትትል ስራው ባሻገር መገናኛ ብዙሃን የሕብረተሰቡን አመለካከትና አስተሳሰብ በመቀየር ረገድ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ተገቢው መረጃ ለሕዝቡ እንዲደርስ መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር ይሰራል ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም