የመደመር ትውልድ መፅሐፍን በመግዛት ልማትን ለማጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ የድሬዳዋ ባለሃብቶች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር ትውልድ መፅሐፍን በመግዛት ልማትን ለማጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ የድሬዳዋ ባለሃብቶች ተናገሩ
ድሬዳዋ ሚያዚያ 24/2015 (ኢዜአ) የመደመር ትውልድ መፅሐፍ ከዕውቀት ባሻገር ከመጽሐፉ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ለልማት ስለሚውል መፅሐፉን በመግዛት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የድሬዳዋ ባለሃብቶች ተናገሩ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ "የመደመር ትውልድ መፅሀፍ" የመተዋወቂያ መድረክ ትናንት በድሬዳዋ ተካሂዷል።
በትውውቅ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተሳተፉት እና አስተያየታቸውን ለኢዜአ የገለጹት ባለሃብቶች እንዳሉት፤ መፅሐፉ ለትውልድ ከሚሰጠው ትምህርት ባለፈ ከመፅሐፉ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ለየአካባቢው ልማት እንዲውል መደረጉ የሚያኮራ ሥራ ነው።
በአገልግሎት እና በመዝናኛ ዘርፍ የተሰማሩት የይገዙ ቤተሰብ ተወካይ አቶ ቤካ ለገሰ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የድሬዳዋን የልማት እንቅስቃሴዎች ለማገዝ የመደመር መፅሃፍን በብዛት በመግዛት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ የበዴይሣ ሪል ስቴት ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዱልለጢፍ መሐመድ በበኩላቸው የዶክተር ዐቢይ መፅሐፍ ለአገር ከፍታ የትውልድን መተባበር እና የአገር መፃኢ ተስፋን የሚያመለክት ዕውቀቶች እና መረጃዎች የተካተቱበት ጠቃሚ መፅሐፍ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላቸውን የተጣበበ ጊዜ በመጠቀም ለትውልድ የሚጠቅም መጽሐፍ በመጻፍ ያሳዩንን ምሳሌ ተከትለን እኛም ለአገር ዘላቂ ልማት መፅሐፉን በመግዛት ኃላፊነታችንን እንወጣለን ብለዋል።
"ዞአ መንግስታዊ ያልሆነ ዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት ማህበራዊ ችግሮችን ለማቃለል በሚከናወኑ ፕሮጀከቶች ውስጥ የራሱን ኃላፊነት መወጣቱን ያጠናክራል" ያለቸው ደግሞ የድርጅቱ የፕሮጀክት አስተባባሪ ወይዘሪት ሜላት ብርሃኔ ናት።
ወይዘሪት ሜላት አክላም፣ ድርጅቱ የመደመር ትውልድ መፅሐፍን በመግዛት የድሬዳዋን ማህበረሰብ የልማት ጥያቄዎች ለማቃለል ተዘጋጅቷል።
የመደመር ትውልድ መፅሐፍ ለማስተዋወቅ የተዘጋጀውን መድረክ የመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከዲር ጁሃር በበኩላቸው፣ ባለሀብቶች የድሬዳዋን ሁለንተናዊ ዕድገት እና ዘላቂ ሰላም በመጠበቅ በኩል ያለባቸውን ኃላፊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
"የመደመር ትውልድ መፅሐፍ" ለትውልዱ አዲስ የአገር ተስፋ፣ ህብረትና አንድነትን የሚያስተምር መሆኑን አስታውሰው፣ "ከመፅሐፍ ሽያጭ የሚገኘው ገንዘብ ለትውልዱ ዕውቀት መቅስሚያነት የሚያገለግል ዘመናዊ ቤተ-መጻህፍት ይገነባበታል" ብለዋል።
ባለሃብቶች ለድሬዳዋ ልማት መጠናከር የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ ማጠናከር እንዳለባቸው ጠቁመው፣ መፅሀፉን በመግዛት አካባቢያቸውን ለማልማት መዘጋጀታቸውን አበረታተዋል።
የአገር የብልፅግና ጉዞን ለማረጋገጥና ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን በሚከናወኑ ሥራዎች ባለሃብቶች እያበረከቱ ያሉትን አስተዋጽኦ ማጠናከር እንዳለባቸው የጠየቁት ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ናቸው።
የአዲሱ ትውልድና የአገር ተስፋ የተመላከቱበት የመደመር ትውልድ መፅሐፍን መግዛት ዕውቀት ማትረፍና የአካባቢን ልማት ማገዝ ነው።
በድሬዳዋ አስተዳደር "የመደመር ትውልድ መፅሐፍ" የሽያጭ ስነ-ስርዓት ለሳምንታት በተቀናጀ መንገድ እንደሚከናወን ለማወቅ ተችሏል።