መንግስት ተጠያቂነትና የሽግግር ፍትሕን ለማረጋገጥ እየሰራ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ተጠያቂነትና የሽግግር ፍትሕን ለማረጋገጥ እየሰራ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ ሚያዚያ 24/2015(ኢዜአ):- መንግስት ተጠያቂነትና የሽግግር ፍትሕን ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
አቶ ደመቀ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ተርክን ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ውይይታቸው የሽግግር ፍትሕ ላይ በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
አቶ ደመቀ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የወሰዳቸውን የተለያዩ እርምጃዎች አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መቋቋሙንና የመልሶ ማቋቋም ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት ለሰላም ስምምነቱ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የተዘጋጀው የእውቅና መርሐግብር ሰላምን ለማስፈን እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው ብለዋል።
መንግሥት ተጠያቂነትንና የሽግግር ፍትሕን ለማስፈን በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝና የሚኒስቴሮች ግብረ ኃይሉ ተቋቁሞ ወደ ተግባር መግባቱ የዚሁ ስራ ውጤት አካል መሆኑን አመልክተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ተርክ በበኩላቸው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን አድንቀዋል።
ቢሯቸው ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶችን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።