እየጣለ ያለው የበልግ ዝናብ በቀጣዩ የግንቦት ወርም ተጠናክሮ ይቀጥላል- የሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
እየጣለ ያለው የበልግ ዝናብ በቀጣዩ የግንቦት ወርም ተጠናክሮ ይቀጥላል- የሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት
አዲስ አበባ ሚያዚያ 24/2015(ኢዜአ):-እየጣለ ያለው የበልግ ዝናብ በቀጣዩ የግንቦት ወርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከባድ ዝናብ የሚያስገኙ የሚቲዎሮሎጂ ክስተቶች ስለሚኖሩ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።
የኢንስቲትዮቱ የሚቲዎሮሎጂ ትንበያና የቅደመ ማስጠንቀቅያ ምርምር ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር አሳምነው ተሾመ፤ ለኢዜአ እንደገለጹት እየጣለ ያለው የበልግ ዝናብ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል።
ለዝናብ መፈጠር አመቺ የሆኑ አየር ሁኔታ ክስተቶች በሀገሪቱ ደቡባዊ አጋማሽ፣ በሰሜን ምስራቅ፣ በመካከለኛው እና በደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ላይ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በእነዚሁ አካባቢዎች ከአነስተኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እና ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊኖር እንደሚችልም ጠቁመዋል።
በተለይ ከአማራ ክልል ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ምዕራብና ምስራቅ ጎጀም፣ ዋግህምራ፣ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር፣ ምስራቅና ደቡብ ትግራይ፣ አፋር ዞኖች ከባድ ዝናብ ሊኖር ይችላል ብለዋል።
በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ፣ ሰሜንና ምስራቅ ሸዋን ጨምሮ ድሬደዋ፣ አዲስ አበባ፣ ሐረሪ፣ ባሌ፣ ምዕራብ አርሲ፣ ቦረና እና ጉጂ በሚቀጥሉት አስር ቀናት ከባድ ዝናብ የሚጠበቅ መሆኑን ዶክተር አሳምነው ገልጸዋል።
ከሀገሪቱ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚዎች መካከል የደቡብ ክልል አጋማሽ፣ የሶማሌ ክልል፣ ሁለቱ ጉጂ ዞኖች፣ ሁለቱ ባሌ ዞኖች፣ ቦረና ዞን፣ ደቡብ ክልል፣ ሲዳማ ክልል፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ተጠቃሽ ናቸው።
በነዚሁ አካባቢዎች በተለይ በሚቀጥሉት አስር ቀናት ከባድ ዝናብ የሚጠበቅ በመሆኑ ከጎርፍና መሰል አደጋዎች ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በሱማሌ ክልል፣ የደቡብ ኦሮሚያ ቆላማ አካባቢዎች ጉጂ፣ ቦረና፣ ከደቡብ ክልል የጂንካ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶና ሌሎች አካባቢዎችም የበልግ ዝናብ በጥሩ ሁኔታ የሚያገኙ አካባቢዎች ናቸው ብለዋል።