ቀጥታ፡

ናይጄሪያ የኢትዮጵያን የስንዴ ምርታማነት ልምድ መጋራት ትፈልጋለች-የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት

አዲስ አበባ ሚያዚያ 24/2015(ኢዜአ)፡- አዲስ የተመረጡት የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማ፤ አገራቸው የኢትዮጵያን የስንዴ ምርታማነት ልምድ የመጋራት ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።

በናይጄሪያ አዲሱ ተመራጭ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማ የተመራው ከፍተኛ ልዑክ በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገውን የስንዴ ምርታማነት ልምድና ተሞክሮ ለመውሰድ የሚያስችል ውይይት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር አድርጓል።

ለልዑካን ቡድኑ ኢትዮጵያ ስንዴን ከውጭ ከማስገባት ነጻ ለመውጣት ያለፈችባቸው መንገዶችና ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶች የተመለከቱ ገለጻ ተደርጓል።


 

ከውይይቱ በኋላ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማ፤ የኢትዮጵያ የስንዴ ልማት ተሞክሮ ለሌሎችም አገሮች መወሰድ ያለበት አስደናቂ ስራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የልማት ስራዎች የሚደነቁ መሆናቸውን ጠቅሰው ናይጄሪያ ልምድ የመጋራት ፍላጎት ስላላት ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከጥቂት አመታት በፊት ስንዴ ከውጭ ስታስገባ ብትቆይም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት የስንዴ ምርት ፍጆታን በአገር ውስጥ ከመሸፈን አልፋ ለውጭ ገበያ ማቅረቧ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በአመት 2 ቢሊዮን ዶላር ስንዴን ከውጭ ለማስገባት ወጪ የምታደርገው ናይጀሪያ የስንዴ ምርታማነትን መጨመር የምትችልባቸውን መንገዶች ከኢትዮጵያ መማር ትፈልጋለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ልማት ያስመዘገበችው ስኬት ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በማደግ ላይ ላሉ የአለም አገሮችም ምርጥ ተሞክሮ እንደሚሆን ጠቁመዋል።


 

የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ፤ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት አመታት በግብርናው ዘርፍ ካስመዘገበቻቸው ለውጦች ልምድ ለመውሰድ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም በአፍሪካውያን ዘንድ መነቃቃትን በመፍጠር ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ ለማምጣት ትልቅ ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ስኬትን ለማስመዝገብ ያለፈችባቸውን ሂደቶች ለሌሎች በማካፈል ድጋፍ ለማድረግም ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።

አፍሪካ በምግብ እራሷን ለመቻል ለምታከናውነው ተግባር መልካም ተሞክሮዎችን መለዋወጡ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም