ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ታሪክ በአግባቡና በተገቢው መልኩ በመሰነድ የአብሮነት ማጠናከሪያና የጋራ ሃብት ማድረግ ይገባል- ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

አዲስ አበባ ሚያዚያ 24/2015(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያን ታሪክ በአግባቡና በተገቢው መልኩ በመሰነድ የአብሮነት ማጠናከሪያና የጋራ ሃብት ማድረግ እንደሚገባ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ገለጹ። 

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አዘጋጅነት በአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ለተከታታይ ስድስት ቀናት የሚቆይ የመጻህፍት አውደ-ርዕይ ተከፍቷል።


 

በአውደ-ርዕዩ ላይ  "የጠቅላይ ሚኒስትር ቋሚ ቤተ-ንባብ" በይፋ ተከፍቷል።

በዚሁ መርሃ-ግብር ላይ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ለንባብ ያበቋቸው መጻህፍት ቀርበዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና በጽሕፈት ቤታቸው ለሕትመት የበቁ ጽሑፎችን የማስተዋወቅ ሥራም  እንደሚካሄድ ተገልጿል።

"ቃል፤ ተግባር፤ ትውልድ" በሚል መሪ ሀሳብ በአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት የተዘጋጀው አውደ-ርዕይ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 29 ቀን 2015 ዓ.ም  የሚቆይ መሆኑም ታውቋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም፤ አውደ-ርዕዩ የማኅበረሰቡን የንባብ ባሕል ለማጎልበት በማለም የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በቤተ-ንባቡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የጹሑፍ ሥራዎች በተጨማሪም፤ በቀጣይ ኢትዮጵያን የሚመሩ የሌሎች ጠቅላይ ሚኒስትሮች ታሪክና የጽሑፍ ሥራዎቻቸው ተሰንደው የሚቀመጡበት ይሆናል ነው ያሉት።

በቋሚ ቤተ-ንባቡ አንባቢያን የሀገር መሪዎች በሥራ ገበታቸው የሚሰሯቸውን ክንውኖችና ሃሳቦች አንድ ቦታ ላይ የሚያገኙበትን ዕድል በመፍጠርና ለትውልድ ለማስተላለፍ እንደሚረዳም ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ አገር የምትመራበት ፖሊሲ የሚወጣው ከመሪዎች በሚመነጭ ሃሳብ ስለሆነ ሁነቶቹም የዘመኑ መገለጫዎች ናቸው ብለዋል።

ታሪካዊ ሁነቶችን በተገቢው መንገድ መሰነድ መቻል ደግሞ የትናንት አገራዊ ታሪክን ለመገንዘብ ከፍተኛ ዕድል እንደሚፈጥርም በመጠቆም።

የኢትዮጵያን የዘመን ታሪካዊ ሃሳብና ድርጊት በተገቢው መንገድ በመሰነድ፤ የአብሮነት ማጠናከሪያና የጋራ ሃብት ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የመሰነድ ዕድል ያላገኙ ታሪካዊ ሁነቶችን በሚገባ መሰነድ ያስፈልጋል  ነው ያሉት ሚኒስትሩ፡፡

የብሔራዊ ቤተ-መጽሐፍትና ወመዘክር ኃላፊ ይኩኑ-አምላክ መዝገቡ፤ እንደ ትርጓሜ መጽሐፍት፣ ቅኔና ዜማ ያሉ ዋና ዋና የኢትዮጵያ ጥበቦች የንባብ ውጤቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።

በመሆኑም የንባብ ባሕልን በማጎልበት ሊደመጥና እንደገና ሊነበብ የሚችል ሥራ መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

በአውደ-ርዕዩ ላይ “ታሪክን ለትውልድ መሰነድ" በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ በተደረገው የውይይት መድረክ ታሪክን በተሟላ አግባብ መሰነድ ለትውልድ ግንባታ የላቀ ሚና  እንዳለው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም