ቀጥታ፡

የጀርመን ትራቭል አሶሴሽን የኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻዎችና አማራጮች በጀርመን ለማስተዋወቅ መዘጋጀቱን ገለጸ

 

አዲስ አበባ ሚያዚያ 24/2015 (ኢዜአ):- የጀርመን ትራቭል አሶሴሽን የኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻዎችና አማራጮች በጀርመን ለማስተዋወቅ መዘጋጀቱን አስታወቀ።

የአሶሴሽኑ ልዑካን ቡድን በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርግም ተገልጿል።

በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍቃዱ በየነ ከጀርመን ትራቭል አሶሴሽን የፖሊሲና የውጪ ቱሪዝም ኃላፊ ቮልከር አዳምስ ጋር ተወያይተዋል።

አምባሳደር ፍቃዱ የጀርመን ትራቭል አሶሴሽን የኢትዮጵያን ቱሪስት መዳረሻዎችን ለጀርመን የቱሪዝም ገበያ በሰፊው ለማስተዋወቅ ለሚያደርጉት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ በ10 ዓመት የመሪ ልማት እቅድ ከተቀመጡ አምስቱ የትኩረት መስኮች አንዱ መሆኑንና በአገር ደረጃ ዘርፉን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የጀርመን ትራቭል አሶሴሽን የፖሊሲና የውጪ ቱሪዝም ኃላፊ ቮልከር አዳምስ የኢትዮጵያን የቱሪዝም አማራጮች ለጀርመን ገበያ ለማስተዋወቅ 14 የጀርመን የጉዞ ወኪሎችና አስጎብኚ ድርጅቶችን የያዘ የልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ጠቁመዋል።

ልዑኩ የቱሪዝም ገበያ ጥናት ፎረም ኢትዮጵያ ላይ ለማካሄድ ማቀዱንም ኃላፊው ለአምባሳደሩ ገልጸውላቸዋል።

የጀርመን ትራቭል አሶሴሽን አመራሮችን ያካተተ ልዑክም የቱሪዝም ጉብኝት በኢትዮጵያ በቅርቡ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።

አሶሴሽኑ በጀርመን በሚገኙ 10 ሺህ የሚደርሱ የጉዞ ወኪሎች አማካኝነት የኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻዎችና አማራጮች ለጀርመን ለማስተዋወቅ ዝግጁ መሆናቸውን ኃላፊው መግለጻቸውን በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

እ.አ.አ በ1950 የተቋቋመው የጀርመን ትራቭል አሶሴሽን በአገሪቷ የቱሪዝም ዘርፍ በዋናነት ከሚጠቀሱ ተቋማት መካከል አንዱ ነው።

አሶሴሽኑ የቱር ኦፕሬተሮችና የጉዞ ወኪሎች ፍላጎትን ወክሎ የሚሰራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም